የአዋሽ ተፋሰስን በዘላቂነት ከጎርፍ አደጋ ለመከላከል የሚያስችል አገራዊ የኢኮኖሚ አቅም አለመኖሩ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የአዋሽ ተፋሰስን በዘላቂነት ከጎርፍ አደጋ ለመከላከል የሚያስችል አገራዊ የኢኮኖሚ አቅም አለመኖሩ ተገለጸ
አዲስ አበባ መስከረም 22/2013 ( ኢዜአ) የአዋሽ ተፋሰስን በዘላቂነት ከጎርፍ አደጋ ለመከላከል የሚያስችል አገራዊ የኢኮኖሚ አቅም አለመኖሩን የኢትዮጵያ ተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ካሉ ተፋሰሶች በተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋ የሚያጋጥመውና ክረምት በመጣ ቁጥር ለአካባቢው ነዋሪዎች ስጋት ከሆኑት መካከል የአዋሽ ተፋሰስ ዋነኛው ነው።
በተፋሰሱ በየጊዜው የጎርፍ መከላከል ሥራዎችን አስቀድሞ ለመስራት ሙከራዎች ቢኖሩም የአዋሽ ወንዝ በሞላ ቁጥር ግን በጎርፍ ምክንያት የአካባቢውን ነዋሪዎች ማፈናቀሉ የተለመደ እየሆነ ከመጣ ሰነባብቷል።
80 በመቶው የአዋሽ ተፋሰስ በተፈጥሮ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆነ አካባቢ መሆኑንም መረጃዎች ያሳያሉ።
በዘንድሮ ክረምትም እንደተለመደው የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ ባስከተለው ጎርፍ በርካታ ዜጎች ከመኖሪያ ቄያቸው ተፈናቅለዋል፤ ቤት ንብረታቸውን ከማጣት ባለፈ በርካታ እንስሳትም ሞተውባቸዋል።
ለመሆኑ በተፋሰሱ ዘለቂ መፍትሄ መስጠት ያልተቻለው ለምን ይሆን ? ሲል ኢዜአ የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዳነች ያሬድን ጠይቋል።
ዳይሬክተሯ እንደሚሉት የአዋሽ ተፋሰስ ጆግራፊያዊ አቀማመጡ ሜዳማ መሆን በራሱ በቀላሉ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ ያደርገዋል።
"ከዚህ ባለፈ አዲስ አበባን ጨምሮ አብዛኞቹ የአገሪቷ ከተሞችን የሚይዝ ተፋሰስ ቢሆንም የወንዝ ማስፋቱ ሥራ በዚያው ልክ አለመሰራቱ ተጋላጭነቱን ያባብሰዋል" ነው ያሉት።
የአዋሽ ተፋሰስን ጨምሮ በሌሎች ተፋሰሶች ላይ የሚሰሩ የወንዝ ማስፋት ሥራዎች ከሚፈለገው አኳያ ውስን መሆናቸውንም ዶክተር አዳነች ገልጸዋል።
''የአዋሽ ተፋሰስን በዘላቂነት ከጎርፍ አደጋ ለመከላከል የሚያስችል አገራዊ የኢኮኖሚ አቅም የለንም'' ብለዋል።
በአዋሽ ተፋሰስ በየዓመቱ የሚደርሰውን የጎርፍ አደጋ ጉዳት ለመቀነስ በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ የሚተገበሩ መፍትሄዎች መቀመጣቸውንም ነው ዳይሬክተሯ የተናገሩት።
ከመፍትሄ አቅጣጫዎቹ ውስጥ በአዋሽ ወንዝ ላይ አዳዲስ ግድቦችን መገንባትና ቀደም ሲል ተገንብተው ወደ ስራ ያልገቡ ግድቦችን ወደ ሥራ ማስገባት ይገኙበታል።
በዘንድሮ ክረምት አዋሽ ወንዝ ሞልቶ በአፋር ክልል ባስከተለው የጎርፍ አደጋ ከ240 ሺህ በላይ ዜጎች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ከ144ሺህ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል።
በእዚሁ አደጋ ከ41 ሺህ ሄክታር በላይ በዘር የተሸፈነ መሬት እንዲሁም ለዘር የተዘጋጀ 18 ሺህ ሄክታር መሬት ለጉዳት የተዳረገ ሲሆን ከ21 ሺህ በላይ የቤት እንስሳት ላይም ጉዳት መድረሱን የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል።