ቀጥታ፡

ሁለት ተቋማት ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ የሚውሉ የሕክምና ቁሶችን ድጋፍ አደረጉ

 አዲስ አበባ  መስከረም 22/2013 ( ኢዜአ)የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ እና የደቡብ ኮርያ ኩባንያው ኤስ.ዲ ባዮሴንሰር ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ የሚውሉ የሕክምና ቁሶችን ድጋፍ አደረጉ። 
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከል የሚውሉ ከ23 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ጥንድ የእጅ ጓንቶችን ነው ድጋፍ ያደረገው።

ይህም ቫይረሱን ለመከላከል በግንባር ቀደምነት ለሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች የሚውል ሲሆን ድጋፉ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያጋጥመውን የሕክምና ቁሳቁስ ለማቃለል ያለመ መሆኑ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ዛፉ ኢየሱስወርቅ ዛፉ የተደረገው ድጋፍ ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም 40 ሚሊዮን ብር የሚያዋጡ የሕክምና ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰው የዛሬውን ጨምሮ ትረስት ፈንድ ከ63 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

የደቡብ ኮርያ ኤስ.ዲ ባዮሴንሰር ኩባንያ ደግሞ ለ20 ሺህ የኮሮናቫይረስ ምርመራ የሚውሉና 200 ሺህ ዶላር ወጪ የተደረገባቸው የኮቪድ-19 አንቲጀን መመርመሪያ መሳሪያዎች ድጋፍ አድርጓል።

በኢትዮጵያ የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ እቴነሽ አብርሃም ኩባንያቸው የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የበኩሉን ድርሻ በማድረጉ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ኩባንያው ድጋፍ ያደረጋቸው የህክምና መሳሪያዎች በዓለም ጤና ድርጅትና በዘርፉ የተቀመጠውን አስፈላጊውን የጥራት ፍተሻ ያለፉና የጥራት ደረጃቸውም የተረጋገጠ መሆኑን ነው ያስረዱት።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው ሁለቱም ተቋማት ላደረጉት ድጋፍ አመስግነው "ድጋፉ ወረርሽኙን ለመከላከል ትልቅ አስተዋጽዖ አለው" ብለዋል።

በተለይም የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ከሚያደርገው የቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ አገራዊ የወረርሽኝ ምላሹ የተሳካ እንዲሆን የማማከር ሥራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

"የደቡብ ኮርያ ኩባንያው "ኤስ.ዲ ባዮሴንሰር" ያደረገው የኮቪድ-19 አንቲጀን መመርመሪያ መሳሪያም ወደፊት ምርመራውን ለማስጀመር ትልቅ ግብዓት ይሆናል" ብለዋል።  

እነዚህ የአነቲጅን ምርመራዎች በዓለም የጤና ድርጅት በቅርቡ ይፋ የሆኑና ዛሬ የተደረገው መመርመሪያ መሳሪያም በዚህ ድርጅት እውቅና የተሰጠው መሆኑም ገልጸዋል።

ሁለቱም ተቋማት እያደረጉ ላሉት ድጋፍና ትብብር ከጤና ሚኒስቴር የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም