ቀጥታ፡

ለችግር የተጋለጡ ከስደት ተመላሾችን ለመደገፍ የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22/2013 (ኢዜአ) በኮቪድ-19 ምክንያት ከተለያዩ አገራት ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ ስደተኞች ውስጥ ለችግር የተጋለጡትን ለመደገፍ የሚያስችል የ217 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ስምምነት ተፈረመ።

ገንዘቡ የኮሮና ቫይረስ መከሰትን ተከትሎ ወደ አገር ከተመለሱ 30ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች ውስጥ ለችግር ለተጋለጡት ድጋፍ ለመስጠት የሚውል መሆኑ ተጠቁሟል።

ስምምነቱን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ የዓለም አቀፉ ፍልሰተኞች ድርጅት የኢትዮጵያ ዋና ኃላፊ ሚስ ሞሪን አቺዬንግ፣ የዓለም ሥራ ድርጅት ተወካይ አይዳ አወል እንዲሁም በኢትዮጵያ የዳኒሽ ሪፊውጂ ካውንስል ዳይሬክተር ሚስስ ኢስቴር ሳቲዋርት ተፈራርመዋል።

በድጋፉ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉትን የስደት ተመላሾች በመምረጥ በግለሰብ ደረጃ ለሦስት ወር 4ሺህ 500 ብር የኪስ ገንዘብ እንደሚሰጥ የተገለፀ ሲሆን የአቅም ግንባታ ስልጠናም በድጋፉ እንደሚካተት ተገልጿል።

በስምምነቱ ላይ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንዳሉት ዜጎች ለሥራ በህጋዊ መንገድ ከአገር መውጣት ሲኖርባቸው በደላሎች ተታለውና በሌሎች ምክንያቶች በህገወጥ መንገድ ሲጓዙ ይስተዋላል።

በህገወጥ መንገድ ወደ ሌላ አገር ሲገቡ እንደወንጀለኛ እንደሚቆጠሩ ጠቁመው፣ መንግስት ለዜጎቹ ከሚሰጠው ትኩረት የተነሳ በኮቪድ-19 አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ባለበት በአሁኑ ወቅት እንኳ ከአገራት ጋር በመነጋገር ስደተኞች ወደአገራቸው እንዲመለሱ በማድረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

ኮሮናቫይረስ ከተከሰተ በኋላ እንኳ ቁጥራቸው 30 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ወደ አገራቸው መግባታቸውን ጠቁመው፣ የገንዘብ ድጋፉ በኮቪድ-19 ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ ስደተኞች ውስጥ ለከፋ ችግር የተጋለጡት ተመርጠው የሚደገፉበት መሆኑን ገልፀዋል።

ድጋፉ አስቸኳይ እርዳታ እንዲያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ ስደተኞቹን ለማቋቋም እንደሚውልም ተናግረዋል።

በስምምነቱ መሰረት የስደት ተመላሾቹን ለመደገፍና ለማቋቋም ፕሮጀክቶቹ ተቀርጸው እንደሚተገበሩ የገለጹት ሚኒስትሯ፣ ለፕሮጀክቶቹ ስኬታማነት የክልል ቢሮዎች እና አጋሮች ተቀራርበው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የገንዘብ ድጋፉን ያደረጉት የዓለም አቀፍ ድርጅት ተወካዮች በበኩላቸው ስደተኞችን መልሶ ለማቋቋምና ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ በአጋርነት ሲሰሩ መቆየቱን ገልፀው፣ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የዳኒሽ ሪፊውጂ ካውንስል ዳይሬክተር ሚስስ ኢስቴር ሳቲዋርትም ሚኒስቴሩ ከአጋሮች ጋር በመሆን ስደተኞችን መልሶ ለማቋቋም እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው፣ በቀጣይም ድርጅታቸው ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2018 እስከ መጋቢት 2020 ድረስ ከ265 ሺህ በላይ ስደተኞች ወደኢትዮጵያ ተመልሰዋል።

ኮሮናቫይረስ መከሰትን ተከትሎም ካለፈው ሚያዚያ ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ 30 ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች ከመካከለኛው ምስራቅና ከጎረቤት አገራት በአየርና በየብስ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።

በኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስ መከሰትን ተከትሎ ከውጭ ወደ አገር ከገቡ ስደተኞች በተጨማሪ የውጭ አገር ሥራና ሠራተኛ በማገናኘት ሥራ ላይ የተሰማሩ 70 ኤጀንሲዎችም ፍቃዳቸውን ለሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር መልሰው የዋስትና ገንዘባቸው እንዲመለስ መደረጉም ተመልክቷል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም