ኢንስቲትዩቱ ለ7 ሚሊዮን ሕጻናት የፖሊዮ ክትባት ሊሰጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢንስቲትዩቱ ለ7 ሚሊዮን ሕጻናት የፖሊዮ ክትባት ሊሰጥ ነው
አዲስ አበባ መስከረም 22/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በመስከረም ወር መጨረሻ 7 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሕጻናት የፖሊዮ ክትባት እንደሚሰጥ አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ የፖሊዮ በሽታ ስርጭትን ለመግታትና ለማጥፋት እንዲሁም የህጻናትን በሽታ የመከላከል አቅም ለማጎልበት ከመስከረም 27 እስከ መስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም የፖሊዮ ክትባት እንደሚሰጥ ገልጿል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ክትባቱ በኢንስቲትዩቱ ቀደም ብለው በተለዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ይሰጣል።
ክትባቱ ከሚሰጥባቸው ክልሎችም ሶማሌ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ እና ሐረሪ ሲሆኑ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞችም በዋናነት ክትባቱ የሚሰጥባቸው ይሆናሉ።
በዘመቻ በሚሰጠው ክትባት በአራቱ ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ 47 ዞኖች እና 334 ወረዳዎች ቤት ለቤት በሚደረግ ጉብኝት 7 ሚሊዮን ህጻናትን ለመከተብ መታቀዱን የተናገሩት።
በመሆኑም ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ከአሁን በፊት ክትባቱን ቢከተቡም ባይከተቡም አሁን የሚሰጠውን የፖሊዮ ክትባት መውሰድ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ የፖሊዮ በሽታን መከላከል የሚቻለው ህጻናት በመደበኛ ክትባት እና በዘመቻ መልክ የሚሰጠውን የማጠናከሪያ ክትባት በአግባቡ እንዲከተቡ በማድረግ ነው ።
ኢትዮጵያ በ2009 ከዋይልድ ፖሊዮ ቫይረስ ነጻ እንደሆነች መረጋገጡን ያስታወሱት ኃላፊው፣ በአጎራባች አገራት የተከሰተውና በክትባት እጥረት የሚመጣው የፖሊዮ ቫይረስ በግንቦት ወር 2011 ዓ/ም በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን መገኘቱን አስታውሰዋል።
ይህ ተመሳሳይ የሆነ የፖሊዮ ዝርያ በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በተመሳሳይ ዓመት መገኘቱንም ኃላፊው አክለዋል።
አቶ አስቻለው እንዳሉት ፖሊዮ የሚከሰትባቸውን ዋና ዋና ምክንያቶች በአካባቢው በቂ የመደበኛ ክትባት አገልግሎት ተደራሽነት እና ተጠቃሚነት ዝቅተኛ መሆን እንዲሁም በከፍተኛ መጠን ክትባትን ማቋረጥ የሚጠቀሱ ናቸው።
ከዚህ በተጨማሪ በየካቲት ወር 2012 ዓ.ም በደቡብ ክልል በተከሰተው የቢጫ ወባ ወረርሽኝ 86 ሰዎች በበሽታው እንደተያዙና አራት ሰዎች መሞታቸውንም ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።
ወረርሽኙ በተከሰተበት ወረዳ በተሰጠው ምላሽ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር መቻሉንም ጠቅሰዋል።
በአካባቢው ለወረርሽኙ ስጋት የሆኑ መንስኤዎች ስላሉ በክልሉ 11 ወረዳዎች እና አንድ የኦሮሚያ ክልል አጎራባች ለሚኖሩ 704 ሺህ ነዋሪዎች በመጪው ጥቅምት ወር ክትባት ለመስጠት የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑም ገልጸዋል።
ለዘመቻው አተገባበር እና ስኬታማነት የሃይማኖት አባቶች፣ የጎሳ መሪዎች፣ የአካባቢ ሽማግሌዎች እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
የክትባት ዘመቻው ህብረተሰቡ እና የክትባት አገልግሎቱን የሚሰጡ የጤና ባለሙያዎች ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያስችሉ ዘዴዎችን በመጠቀም እንደሚከናወንም ተገልጿል።