ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ዓለም አቀፍ ሽልማት አገኘ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22/2013 (አዜአ) የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ለሰባተኛ ጊዜ የተካሄደውን የ2020 ''የዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሽልማት'' መሸለሙን አስታወቀ።

የባንኩ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር መነን አያሌው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከቱት ባንኩ ሽልማቱን ያሸነፈው በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ኮንኮርዲያ በተባለ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅትና በቨርጂኒያ ዩኒቨርሲቲ በተደረገ ውድድር ነው።

ባንኩ ሽልማቱን ያሸነፈው  በብሌን ንቅለ ተከላ ላይ ለማህበረሰቡ በሚያበረክተው አስተዋጽኦና የአገልግሎት ጥራቱ ከ97 በመቶ በላይ በማስመዝገቡ ነው ብለዋል።

በተጨማሪም የትምህርትና የምርምር ተቋም በመሆን ባለሙያዎችን ማፍራቱ ለሽልማት እንዳበቃው ዶክተር መነን አስታውቀዋል።

ሽልማቱን ዓይን ባንኩ በቀጣይ ስኬታማ ሥራዎችን ለማከናወንና ተደራሽነቱን ለማስፋት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርለትም ተናግረዋል።

ባንኩ የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላን በሚመለከት የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማስፋት መስራት ይጠበቅበታል ያሉት ሜዲካል ዳይሬክተሯ፣ በአገሪቱ እስካሁን ተደራሽ የሆኑት 2ሺህ400 ዜጎች መሆናቸውን ይገልጻሉ።

በአገሪቱ  ከ14 ዓመታት በፊት በተደረገ  ጥናት ከ300ሺህ በላይ የብሌን ንቅለ ተከላ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች  እንደነበሩ በማስታወስ።

በአሁኑ ወቅት ብሌን የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ቁጥር ከዚያ ስለሚልቅ ተደራሽነቱን ማሳደግ ያስፈልጋል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዓይን ህክምና ትምህርት ኃላፊ ዶክተር ሳዲቅ ታጁ በበኩላቸው ኢትዮጵያ 170 የዓይን ሐኪሞች ያሏት ሲሆን፣ የዓይን ሕክምናና ሐኪም የሌለባቸው አፋር፣ጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች መኖራቸውን አንስተዋል።

ይህም በአፍሪካ የዓይን ሕክምና ዘርፍ አነስተኛ ባለሙያዎች ካላቸው አገሮች መካከል ተርታ እንደሚያሰልፋት ገልጸዋል።

በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ለማቃለል የሐኪሞችን ቁጥር መጨመርና  አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልጋትም ኃላፊው ተናግረዋል።

ባንኩ ባለሙያዎችን በማብቃት ረገድ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ማጠናከር እንደሚገባው አመልክተዋል።

በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኙ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ባንኩን በዕውቀት፣ በግብዓቶችና በፋይናንስ ለመደገፍ ቃል ገብተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም