ቀጥታ፡

የኢሬቻ በዓልን ከሌሎች ብሔር ቤሔረሰቦች ጋር በአንድነት እናከብራለን---የበዓሉ ተሳታፊዎች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22/2013(ኢዜአ) የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያዊያን በመሆኑ ከሌሎች ብሔር ቤሔረሰቦች ጋር በአንድነት እንደሚያከብሩት የበዓሉ ተሳታፊዎች ገለጹ።

በኦሮሞ ብሔር የገዳ-ስርዓት ውስጥ ትልቅ ስፍራ ተሰጥቷቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፉ ከመጡ በዓላት መካከል አንዱ የኢሬቻ በዓል ነው።

 የኦሮሞ የገዳ-ስርዓት አዋቂው ሃዩ ደረጀ በሻ እንደሚሉት፣ ኦሮሞ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር ለመኖር አስቀድሞ የመሰረታቸው በርካታ እሴቶች አሉት ብለዋል።

 በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በየዓመቱ የሚከበረው የኢሬቻ በዓልም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ዘንድ እየታወቀ መምጣቱን ሃዩ ደረጀ በሻ ተናግረዋል።

 "ኢሬቻ አምላክን የምንለምንበት ደግሞ የምናመሰግንበት በዓል እስከሆነ ድረስ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ቅርስና ኩራት ነው" ያሉት ሃዩ ደረጀ፣ የበዓሉን እንግዶች ከመዲናዋ ነዋሪዎች ጋር በመሆን መቀበል እና አብሮ ማክበር ይጠበቃል ብለዋል።

 ወይዘሮ ተዋበች ለገሰ በበኩላቸው ፣ '' የበዓሉ ትርጓሜ ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት በመሆኑ ፈጣሪን የተጣለውን አስታርቅልን፣ የተራራቀውን አንድ አድርግልን እያልን ከሌሎች ጋር በጋራ እናከብረዋለን '' ሲሉ ገልጸዋል።

  የኢሬቻ በዓል በዓመት ሁለት ጊዜ የሚከበር ሲሆን አንደኛው ክረምት ሳይገባ የኦሮሞ ማህበረሰብ ወደ ተራራማ ስፍራ በመሄድ አምላኩን የሚለምንበት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ክረምት ሲወጣ አምላኩን ለማመስገን የሚያከብረው ነው።

 እንደ ኢሬቻ ሁሉ በገዳ-ስርዓት ውስጥ ከሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር በሔረሰቦች ጋር አብሮ ለመኖር ከሚታወቁ እሴቶች መካከል ''ጉዲፈቻ'' ''ሞጋሳ'' እና  ''ሃርማ ሆዳ'' ይጠቀሳሉ።

ኢሬቻ ከገዳ ሥርዓት መገለጫዎች አንዱ ሲሆን የአንድነት፣ የፍቅር፣ የአብሮነትና ሰላም መገለጫ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም