ለሀገር ሰላምና ልማት በበለጠ በጋራ እንሠራለን -ርዕሳነ መስተዳደሮች - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገር ሰላምና ልማት በበለጠ በጋራ እንሠራለን -ርዕሳነ መስተዳደሮች
ሐዋሳ፣ መስከረም 22/2013 (ኢዜአ) - በለውጥ ሂደቱ በርካታ ፈተናዎች ቢያጋጥምም ካለፍንባቸው መሰናክሎች ልምድ በመውሰድ ለሀገር ሰላምና ልማት በበለጠ በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን የሲዳማ፣ የደቡብና የኦሮሚያ ክልል ርዕሰነ መስተዳድሮች አስታወቁ።
ርዕሳነ መስተዳድሮቹ ይህን ያስታወቁት በደቡብ ክልል ለሰላምና መረጋጋት የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ትላንት በሐዋሳ ዕውቅናና ምሥክር ወረቀት በተሰጠበት ሥነ-ሥርዓት ላይ ነው።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በወቅቱ እንደገለጹት የኢትዮጵያን ሕዝቦች አንድነትና ሰላም የማይፈልጉ ኃይሎች ቢኖሩም ሰላሟንና አንድነቷን ማስቀጠል የሚችሉ ልጆች ያሏት በመሆኑ አይሳካላቸውም።
በደምና አጥንት የተገመደ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ወንድማማችነት እየጠነከረ የሚሄድ መሆኑን አመላክተዋል።
"ከትናንት ውድቀታቸው የማይማሩና ቀን እየቆረጡ ኢትዮጵያን የሚያፈርሱ የሚመስላቸው ኃይሎች ራሳቸው ይጠፋሉ እንጂ ኢትዮጵያ ፈጽሞ አትፈርስም" ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ቀጣይ መንገድ እኩልነት፣ ዴሞክራሲ፣ ነፃነት፣ወንድማማችነትና ፍትሕ የሚረጋግጥበት እንጂ አንዱ የበታች ሌላው የበላይ የሚሆንበት እንዳልሆነ አቶ ሽመልስ አስታውቀዋል።
የሀገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች አንድነታቸውን በማጥበቅ ሀገር ለማፍረስ መጠራጠርን የሚዘሩ ኃሎችን መታገል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
የኦሮሚያ ክልል ከደቡብ ክልል ጋር በመሆን ሰላምና ልማትን ለማስቀጠል አስፈልጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው "ጥያቄዎችን በሰከነ መንፈስ፣ በመነጋገርና በሰላማዊ መልኩ የመፍታት ልምድን ለማስቀጠል የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ሌጋሲ አርዓያችን ሊሆን ይገባል" ብለዋል።
"ከአባቶች እንደተማርነው የባሕል፣ ቋንቋና መሰል ልዩነቶች በተፈጥሮ የተቸረን ፀጋችንና የውበታችን መገለጫ እንጂ የጥል መነሻ ሊሆነን አይገባም" ሲሉም ተናግረዋል።
"ለዘመናት የቆዩ ችግሮቻችንን በመነጋገር ደረጃ በደረጃ እየፈታን የሀገራችንን ብልፅግና ለማፋጠን በምናደርገው ጥረት ልዩነትን በመስበክ አንድነታችንን ለመፈታተን የሚሞክሩ ኃይሎች ሴራን ለማክሸፍ ሰላማችንን መጠበቅ ወሳኝ ነው" ብለዋል።
የኮሮና ቫይረስ ያሳደረውን ተፅዕኖ በመቋቋም የሀገሪቱን ልዕልና ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት በአቋራጭ ሥልጣን ለመያዝና ከሰላም መደፍረስ ትርፍ ለማግኘት የሚሯሯጡ ኃይሎችን ለማስታገስ ሕዝቡ በንቃት ሰላሙን ሊጠብቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በውስጥም ሆነ በውጭ ጠላት የማትደፈር፣ ጠንካራ፣ ሰላሟ የተጠበቀና የተጀመረውን የብልፅግና ጉዞ የምታሳካ ሀገር ለመገንባት ሁሉም አንድነቱን በማጠናከር ሊታገል እንደሚገባ አቶ ደስታ አስታውቀዋል።
"በተጀመረው የለውጥ ጉዞ ሀገራችንን ወደ ከፍታ ለማሻገር የሚቻለው ለሰላም ቅድሚያ ተሰጥቶ ሲሠራ ነው" ያሉት ደግሞ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ናቸው።
ለተግባራዊነቱ ከቤተሰብ ጀምሮ በየደረጃው በሚገኙ መዋቅሮችና ተቋማት የሰላም ግንባታ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸው አመላክተዋል።
በሕዝቡ ውስጥ በመሰግሰግ ሰላምን ለማደፍረስ የሚጥሩ ኃይሎችን ሴራ ለማክሸፍና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ይበልጥ በመቀራረብ እንደሚሠራ አቶ ርስቱ አረጋግጠዋል።
የሕዝቦችን አንድነትና ሰላም በማረጋገጥ ለሀገሪቱ ቀጣይነት በጋራ እንደሚሠሩ ርዕሳነ መስተዳድሮቹ አስታውቀዋል።