በምዕራብ ወለጋ ከ42 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነቡ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተቋማት ለአገልግሎት በቁ - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ወለጋ ከ42 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነቡ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተቋማት ለአገልግሎት በቁ
ነቀምቴ፣ መስከረም 22/2013 (ኢዜአ) በምዕራብ ወለጋ ዞን መንግስት በመደበው ከ42 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተገነቡ ንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ለአገልግሎት መብቃታቸውን የዞኑ የውሃ ሀብት ልማትና ኢነርጂ ጽህፈት ቤት ገለጸ።
ምንጭ ማጎልበት ፣ ጥልቅና መካከለኛ የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ ከተጓዳኝ መገልገያዎች ጋር ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁት ከ200 በላይ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተቋማት እንደሆኑ ተመልክቷል።
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዘሪሁን ጎበና እንዳሉት በ2012 የበጀት ዓመት ውስጥ በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የተገነቡት የውሃ ተቋማቱ ከ130 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።
ንጹህ የመጠጥ ውሃ ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች የተገነቡት እነዚህ የውሃ ተቋማት የዞኑ የውሃ ሽፋንም ከነበረበት 78 ነጥብ 6 በመቶ ወደ 81 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በዞኑ ነጆ ወረዳ የወሊታቴ ቀበሌ አርሶ አደር መሐመድ ሁንዴሳ በሰጡት አስተያየት በቀበሌያቸው በንጹህ የመጠጥ ውሃ ችግር ንጽህናው ያልተጠበቀ ውሃ በመጠቀም ለውሃ ወለድ በሽታ ተጋልጠው መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡
በአቅራቢያቸው ተገንብቶ በቅርቡ ለአገልግሎት የበቃው የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋም የነበረባቸው ችግር መቃለሉን ተናግረዋል።
ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር ዲልጋሣ ፉፋ በበኩላቸው በቀበሌው በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የውሃ ማመንጫ ተገንብቶላቸው ባሉበት አካባቢ በተመቻቸላቸው አራት የውሃ ቦኖዎች አገልግሎት ንጹህ የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪ የልብስ ማጠቢያና የገላ መታጠቢያ ተገንብቶላቸው ለአገልግሎት እንደተመቻቸላቸውም ጠቅሰዋል፡፡