የአለም ከተሞችን የሚያገናኘው አለም አቀፉ የከተሞች ወር በመጪው ወር ይከበራል

88

አዲስ አበባ፣ መስከረም 21/2013 ( ኢዜአ)  የአለም ከተሞችን የሚያገናኘው አለም አቀፉ የከተሞች ወር ጥቅምት 5 መከበር ይጀምራል፡፡

የዘንድሮው "አርባን ኦክቶበር" እ.ኤ.አ ጥቅምት 5 ቀን 2020 በኢንዶኔዥያ ሱራባያ ከተማ "የመኖሪያ ቤቶች ለሁሉም ወደ ፊት የተሻሉ ከተሞች" በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል፡፡

"አርባን ኦክቶበር" ከተሞች ያሏቸውን መልካም ዕድሎችና ተግዳሮቶች እንዲሁም ቀጣይ አቅጣጫዎች በተመለከተ ዜጎች የከተማ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እንዲወያዩ የሚያደርግ የ30 ቀናት ዘመቻ የሚደረግበት ወር ነው፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየዓመቱ ጥቅምት ወር የዓለም አገራት በከተሞች ጉዳይ ላይ የሚመክሩባቸውን አጀንዳዎች በማመላከት ለከተሞች ትኩረት እንዲሰጡ የሚረዱ የተለያዩ ፕሮግራሞች እንዲያካሄዱ ያደርጋል፡፡

በተጠቀሰው ወር አገራት፣ ከተሞች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ምሁራንና የከተማ ነዋሪዎች የተለያዩ መድረኮችን በመጠቀም ውይይትና ክርክር ያከናውናሉ፡፡

በዚህም በዓለም በፍጥነት እየተስፋፋ የመጣውን ከተሜነት በተመለከተ ሰፋ ያለ ምክክር እንደሚደረግበት የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የዓለም መሪዎች እ.ኤ.አ በ2015 ያስቀመጡትን ከተሞች ሁሉን አቀፍ፣ ደህንነታቸው የተጠበቀ፣ ጠንካራ የመቋቋም አቅም ያላቸው እንዲሆኑ ለማስቻል የተቀመጡትን 11 ግቦች ለመተግበር ምክክሩ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው ተገልጿል፡፡

በዓሉ በኢትዮጵያ በ10 ዓመት መሪ ዕቅድ ማስተግበሪያ ጉባኤ፣ የከተሞች ከንቲባዎች ምስረታ፣ የከተሞች አጋርነት ትብብር ፎረም ጉባኤ በከተሞች ሰላምን ለማረጋገጥ የሴቶች ሚና እና በከተሞች የመልካም ተሞክሮ ጉብኝት እንደሚከበር ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም