ለመምህርነት ሙያ ተገቢውን ክብርና እውቅና ለመስጠት ይሰራል -- ትምህርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ለመምህርነት ሙያ ተገቢውን ክብርና እውቅና ለመስጠት ይሰራል -- ትምህርት ሚኒስቴር
አዲስ አበባ መስከረም 21/2013 (ኢዜአ) ለመምህርነት ሙያ ተገቢውን ክብርና እውቅና በመስጠት የመምህራንን ፍላጎት ለማሟላት እንደሚሰራ የትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።
የመምህራን ቀን ከመስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ወር በተለያዩ ዝግጅቶች የሚከበር መሆኑም ታውቋል።
እለቱን በማስመልከት የትምህርት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር በዛሬው እለት በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ገረመው ሁሉቃ በሰጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ ባለፉት 30 ዓመታት ለመምህርነት ሙያ በሚገባው ለክ ክብርና እውቅና አልተሰጠውም ብለዋል።
የመምህራን ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከበረ በኢትዮጵያ ከመምህራን ማህበርና ከክልሎች ውጭ በመንግስት ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶ እስካሁን ሳይከበር መቆየቱንም ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ ግን መምህራን ተገቢውን ክብርና እውቅና እንዲያገኙ ለማድረግ እለቱ በመንግስት ደረጃ እንደሚከበር ዶክተር ገረመው ገልጸዋል።
እለቱን የመምህራንን ስምና ዝና ከፍ በሚያደርጉ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ከማክበርም ባለፈ መንገዶችና አደባባዮች በመምህራን ስም እንዲሰየሙ ይደረጋል ብለዋል።
የመምህርነትን ሙያ ማክበርና እውቅና መስጠት ቅድሚያ የሚሰጠው ቢሆንም የመምህራንን መሰረታዊ ጥያቄና ፍላጎት ማሟላት ደግሞ ለነገ የማይባል ነው ብለዋል።
በተለይም ከደሞዝ ማስተካከያ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጉዳይ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ቢዘገይም በቅርቡ ምላሽ ያገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዘዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲ በበኩላቸው የመምህራን ቀን ሲከበር በስራ ላይ ያሉትን ማበረታታት ብቻ ሳይሆን በጡረታ የወጡትም ይታወሳሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምሩ ከ600 ሺህ በላይ አባላት ያሉት አንጋፋ ተቋም ነው።
የመምህራን ቀን ለመምህርነት ሙያ ተገቢውን ክብርና እውቅና ለመስጠት ከመስከረም 20 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ወር ይከበራል።