ቀጥታ፡

የኤርትራ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሐዋሳ ገብተዋል

አዲስ አበባ ሐምሌ 7/2010 የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን ለመጎብኘት ሐዋሳ ገብተዋል። ፕሬዝዳንቱ ሐዋሳ አየር ማረፊያ ሲደርሱ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የሐይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የከተማዋና አካባቢዋ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። የኢንዱስትሪ ፓርኩን ለማስጎብኘት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ከፕሬዚዳንቱ ጋር ሐዋሳ ይገኛሉ። ለሶስት ቀናት በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት የሚያደርጉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ነገ በሚሌኒየም አዳራሽ ከህዝብ ጋር በሚኖራቸው መድረክ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ምንም እንኳ የአንድ አገር ዜጎች ሆነው የቆዩ ቢሆንም፤ በ1985 ዓ.ም በተደረገው የህዝብ ውሳኔ ኤርትራ ሉዓላዊ አገር መሆን ችላለች፡፡ ብዙም ሳይቆይ በ1990ዎቹ አካባቢ በድንበር ይገባኛል ጥያቄ የተነሳ ወደ ጦርነት ማምራታቸው ይታወሳል፡፡ በተለይም ባለፉት 20 ዓመታት ሰላምም ጦርነትም በሌለበት ሁኔታ መቀጠላቸው በአገራቱ ሕዝቦች ላይ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያና ፖለቲካዊ ተጽእኖ ሲያደርስ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም