ኤጀንሲው በ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጪ ሕንጻ ሊገነባለት ነው

87

አዲስ አበባ መስከረም 13/2013 (ኢዜአ) - ለሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ኤጀንሲ ዋና መሥሪያ ቤት ባለ 21 ፎቅ ለመገንባት ሥምምነት ዛሬ ተደረገ።

በአዲስ አበባ ከተማ ሜክሲኮ አደባባይ የሚገነባው ሕንፃ 1 ነጥብ 64 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚፈጅ ተገልጿል።

ሥምምነቱን የፌዴራል መንግሥት ሕንፃዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤትና የኤጀንሲው ኃላፊዎች ተፈራርመዋል።

ግንባታው በአራት ዓመታት ውስጥ የሚከናወነው ሕንፃ በዓይነቱ የመጀመሪያው እንደሚሆን ተመልክቷል።

ሕንፃው ዋና መሥሪያ ቤቱን ጨምሮ 14 ቅርንጫፎቹን በማሰባሰብ ለኅብረተሰቡ በአማካይ ሥፍራ  ተገንብቶ አገልግሎት እንደሚሰጥ ተገልጿል።  

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ ተቋሙ በፊርማው ሥምምነት ላይ ለዋና መሥሪያ ቤቱና ለ14 ቅርንጫፎቹ በዓመት 40 ሚሊዮን ብር ኪራይ እንደሚከፍል ገልጸዋል።


ግንባታው ከመሬት በታች አራት ወለሎች የሚኖሩት ሲሆን ከመሬት በላይ 21 ወለል እንዳለውና በአራት ዓመት ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚጀምር ተናግረዋል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ በዚሁ ወቅት መንግሥት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከ60 የሚበልጡ ተመሣሣይ ሥራ ለሚያከናውኑ ተቋማት ተመሣሣይ ንድፍ ያላቸውና የሕንፃ አዋጅ ያከበረ ሕንፃ ባለቤቶች ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

የፌዴራል መንግሥት ሕንፃዎች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የተዋቀረ ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም