በ3 ከተሞች ከ53 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የተገነቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ዛሬ ተመረቁ - ኢዜአ አማርኛ
በ3 ከተሞች ከ53 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የተገነቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ዛሬ ተመረቁ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21/2013(ኢዜአ) በቢሸፍቱ፣ ዱከምና በሞጆ ከተሞች ከ53 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገነቡ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ዛሬ ተመርቀዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎቹን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ መርቀው ከፍተውታል።
ከአዲስ አበባ በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት በዱከም ከተማ የተገነባው ባለ 230/15 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የግንባታ፣ ፍተሻና የሙከራ ሥራው ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቁ ተገልጿል፡፡
ከአዲሱ የቢሾፍቱ 400 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ተነስቶ እስከ ዱከም ማከፋፈያ ድረስ 16 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ጥንድ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መሥመር ዝርጋታም ተከናውኗል፡፡
በሞጆ ከተማ የተገነባው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያም በተመሳሳይ ግንባታ፣ ፍተሻና ሙከራው ሙሉ በሙሉ ተጠናቋል፡፡
የዱከምና የሞጆ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ጥንድ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ገቢ መሥመርና 10 ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መሥመሮች ያሏቸው ሲሆን፣ ሁለት ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመሮች ተተክለውላቸዋል፡፡
የጣቢያዎቹ ግንባታ በሕንድ፣በቦስኒያ ሄርዞጎቢኒያና በኢትዮጵያ ሥራ ተቋራጮች መካፈላቸው የታወቀ ሲሆን በአማካሪነት ደግሞ የጀርመንና ስዊዘርላንድ ኩባንያዎች ተሳትፈውበታል፡፡
ግንባታው 85 በመቶ ከፈረንሳይ ልማት ባንክ በተገኘ ብድርና በኢትዮጵያ መንግሥት 15 በመቶ ወጪ መከናወኑ ተገልጿል፡፡
ከፍተኛ የኃይል ጫናና መቆራረጥ ችግሮችም እንደሚቀንሱ የተነገረላቸው ጣቢያዎች ለከተሞቹና አካባቢያቸው እንዲሁም በዙሪያቸው ለሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የኃይል ፍላጎት ምላሽ ለማሟላት የተገነቡ ናቸው፡፡