ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ለመማር ማስተማሩ ስራ ዝግጅት እያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ለመማር ማስተማሩ ስራ ዝግጅት እያደረገ ነው
መቀሌ መስከረም 21/2013 (ኢዜአ) ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የ2013 የትምህርት ዘመን መደበኛ የመማር ማስተማሩ ስራ ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ መሆኑ አስታወቀ።
የዘመኑን የመማር ማስተማር ስራ የሚጀምረው ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስችሉ ጥንቃቄዎችን በመተግበር እንደሆነ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ዛይድ ነጋሽ ለኢዜአ ገልጸዋል።
ለዚህም ግቢውን የማፅዳትና የማስዋብ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው የተማሪዎች ማስተማሪያና መኝታ ክፍሎችም እንደዚሁ እየተዘጋጁ እንደሚገኙ አስረድተዋል።
ከምግብና ንጹህ መጠጥ ውሃ ጋር የተያያዙ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችም እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
ኮሮናን ለመከላከል በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ የነበረ ማቆያና ህክምና ማዕከልም እየተገነባ ባለው ሁለተኛው የተቋሙ ግቢ ተዛውሮ ለተሻለ አገልግሎት እንደሚመቻችም ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ሐየሎም ካህሳይ በበኩላቸው፣የመማር ማስተማር ስራው ሲጀመር ለጥንቃቄ እያንዳንዱ ተማሪ ርቀቱን እንዲጠብቅ፣ የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እንዲጠቀም የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል።
''ባልተሟላ ጤና ጤናማ የመማር ማስተማር ስራውን ማሳካት አይቻልም፤እያንዳንዱ ተማሪና አስተማሪ በትክክል ይህንን ተገንዝቦ የመከላከል ስራውን ተግባራዊ እንዲያደርግ የግንዛቤ ትምህርትና የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያመጣ ይሰራል፤ የማያቋርጥ ክትትልም ይደረጋል''ብለዋል።
የዓዲግራት ከተማ ነዋሪው የአንደኛ ዓመት የኬሚካል ምህንድስና ተማሪ ወጣት ተስፋአለም ተክላይ በሰጠው አስተያየት ''መደበኛ ትምህርት ይጀመራል በመባሉ ደስታ ተሰምቶኛል''ብሏል።
በሚመለከታቸው አካላት የሚሰጠው የጤና መመሪያ ተግባራዊ እያደረገ ትምህርቱን ለመከታተልም ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል።
ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የሚያስተምራቸው ከ20 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንዳሉት ተመልክቷል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ዶክተር ሳሙኤል ሁርካቶ በቅርቡ እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲዎች ትምህርት ለማስጀመር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ ነው።
ግብረ ኃይሉ በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር ዩኒቨርሲቲዎች እያደረጉ ያሉትን ዝግጅት የመስክ ምልከታ እንደሚያካሄድ ጠቁመዋል።
"በመስክ ምልከታው በቂ ዝግጅት እንዳደረጉ በተለዩ ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ የመማር ማስተማር ስራውን እንጀምራለን"ብለዋል።
ከኮሮና ቫይረስ ጥንቃቄዎች ባሻገር በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሁኔታ እንዲኖር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትሩ መግለጻቸውን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል።