የእሬቻ ማክበሪያ ቦታ ጽዳት ተካሄደ

56

አዲስ አበባ መስከረም 21/2013 (ኢዜአ) የእሬቻ በዓል ታዳሚዎች ጽዱ በሆነ ቦታ በዓላቸውን ለማክበር የሚያስችል የእሬቻ ቦታ ጽዳት ተካሄደ። 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመጪው ቅዳሜ መስከረም 23 ቀን 2013 ዓ.ም ለሚከበረው የሆራ ፊንፊኔ እሬቻ በዓል በርካታ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት በማከናወን ላይ ነው።

ዛሬ በተካሄደው የጽዳት ዘመቻና የፀረ ተህዋሲያን ኬሚካል ርጭት ላይ የተገኙት የከተማ አስተዳደሩ የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር እሸቱ ለማ እንደተናገሩት የጽዳት ዘመቻው የተከናወነው የበዓሉ ታዳሚዎች ጽዱ በሆነ ቦታ በዓላቸውን እንዲያከብሩ ለማድረግ ነው።

በጽዳት ስራው ላይ ከከተማው የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን ይሔም በዓሉ የአብሮነት መገለጫ መሆኑን እንደሚያመላክት ገልጸዋል።

የከተማው የከንቲባ ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴከሬተሪያት ኃላፊ ወይዘሮ አልፊያ የሱፍ በበኩላቸው በዓሉን ሲከበር ለኮቪድ-19 ጥንቃቄ አባ ገዳዎች ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት ብቻ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

ዛሬ ከተከናወነው ጽዳት ባለፈ ለበዓሉ የማክበሪያ ቦታ የይዞታ ማረጋገጫ ከመስጠት ጀምሮ በአባገዳዎች አማካኝነት ስለበዓሉ ለወጣቶች ግንዛቤ መስጠትና እንግዶች የሚስተናገዱበትን መርሃ-ግብር ማዘጋጀት እንዲሁም መሰል የዝግጅት ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም