ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ትርፍ ማስገኘት አልቻለም

አዲስ አበባ  መስከረም 20/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በ2012 በጀት ዓመት ትርፍ ያላስገኘ የመንግስት ልማት ድርጅት መሆኑን የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኮርፖሬሽኑ በበጀት ዓመቱ ለኤጀንሲው ተጠሪ ከሆኑ 21 የመንግስት ልማት ድርጅቶች ብቸኛው ትርፋማ ያልሆነ ድርጅት መሆኑም ተገልጿል።

የመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ የ2012 በጀት ዓመት የእቅድ አፈጻጸምና የ2013 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች በተመለከተ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ በየነ ገብረመስቀል ባለፈው በጀት ዓመት ለኤጀንሲው ተጠሪ ከሆኑ 21 የመንግስት የልማት ድርጅቶች 20ዎቹ ከታክስ በፊት 55 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ትርፍ እንዳስገኙ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ባለፈው በጀት ዓመት ኪሳራ ያስመዘገበ ድርጅት መሆኑን ገልጸው፤ ''የስኳር የልማት ዘርፉ ከነበሩበት ችግሮች አኳያ ኮርፖሬሽኑ ትርፍ ያስገኛል ተብሎ አልተጠበቀም'' ብለዋል።

ትርፍ ባያመጣም ኮርፖሬሽኑ 10 ቢሊዮን ብር ያህል ሽያጭ ማስገኘቱንም አመልክተዋል።

የስኳር ፋበሪካዎችን አቅምና ምርታማነት የማሳደግ ስራዎች በመንግስት እየተከናወነ እንደሚገኙና የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል ይዞታ የማዘዋወር ስራን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ለኤጀንሲው ተጠሪ የሆኑ የልማት ድርጅቶች ለረጅም ጊዜ የተጎተቱ ፕሮጀክቶች የአፈጻጸም አቅምን በማሳደግ እንዲጠናቀቁ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

የስኳር ልማት ፕሮጀክት በአፈጻጸም አቅም ማነስ፣ በፕሮጀክቶች መጓተት በብልሹ አሰራሮች ምክንያት ኢትዮጵያን ብዙ ሃብት ያሳጣ ዘርፍ ነው።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በመንግስት በተደረጉ ማሻሻያዎች የተወሰኑ ፋብሪካዎች ስኳር የማምረት አቅማቸው እየተሻሻለ መምጣቱን የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ይገልጻል።

በተለይም ፊንጫና መተሐራ የስኳር ፋብሪካዎች በማምረት አቅማቸው የተሻለ አፈጻጸም ካሳዩ ፋብሪካዎች መካከል ይገኙበታል።

በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት የስኳር ፋብሪካዎች 3 ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ማምረታቸው ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የተወሰኑ የስኳር ፋብሪካዎች ከስኳር ውጪ ኢታኖል እያመረቱ ይገኛሉ።

ተንዳሆ፣ ኦሞ ኩራዝ፣ አርጆ ዴዴሳ፣ ኦሞ ኩራዝና ከሰም በ2013 በጀት ዓመት ወደ ግል ይዞታ ለማዘዋወር እቅድ ከተያዘላቸው የስኳር ፕሮጀክቶች መካከል ይገኙበታል።

መንግስት የስኳር ፋብሪካዎቹን ወደ ግል ይዞታ የማዘዋወር ሂደት በጥንቃቄ የተጠናና የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት እድገት በሚያረጋገጥ መልኩ እንደሚከናወንና የሚደረገው የማዘዋወር ሂደት የግል ዘርፉን በማነቃቃት የአገሪቷን ምጣኔ ሀብት እድገት ፋይዳ እንዳለው ሲገልጽ ቆይቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም