ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ አዲስ ምዕራፍ

አዲስ አበባ ሐምሌ 7/2010 የአሁኗ ዘመናዊት ኤርትራ በቀድሞ በኢትዮጵያ ቀደምት የአክሱም ዘመነ መንግሥት ሥር ቢያንስ ከሦስት መቶ ዓመታት በላይ ሥር ቆይታለች፡፡ ከአክሱም ሥልጣኔ መውደቅ በኋላም በተለያዩ አጋጣሚዎች የኦቶማን ተርክሽ በምጽዋ ላይ የጦር ሰፈር የገነቡ ሲሆን አረቦችም ጭምር በቦታው ላይ ሰፍረዋል። እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1890 ከምዕራብያኖቹ የቅኝ ግዛት የበርሊን ስምምነት በኋላ ይህ ስፍራ በጣሊያን ይዞታ አስተዳደር ሥር ወደቀ። ከዛም ኤርትራ የሚለው ስም ለስፍራው እንደተሰጠና ኤርትራ የሚለው ቃልም የግሪክ ቃል ሲሆን በጣሊያንኛ ትርጓሜው ቀይ መሬት ማለት ነው። ይህም ቀይ ባህር አካባቢ ያለችውን መሬት ለመጠቆም ሲሆን ጣልያንም ስፍራውን የተቆጠጣረችው ኢትዮጵያውያን ለመውረር ማቅዷን ተከትሎ ነው። ይሁንና ጣሊያኖቹ በአጤ ምንሊክ መሪነት አድዋ ላይ ሽንፈትን አስተናግደዋል፤ ይህም ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቁር ሕዝቦች በነጮች ላይ የተቀዳጁት የጦርነት ድል ሆኖ ተመዝግቧል። ይሁንና ኤርትራ በጣሊያኖች ቁጥጥር ሥር ውላ፤ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1941 ለአምስት ዓመታት በእንግሊዝ ሥር ወድቃለች። ከዛም በኋላ እ.ኤ.አ 1949 በመንግሥታቱ ድርጅት የአደራ አስተዳደር ሥር እንድትሆን ተደርጋም ቆይታለች። በመቀጠል እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1952 ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር በፌደሬሽን እንድትጠቃለል የመንግሥታቱ ድርጅት ውሳኔ አሳለፈ። ይህንንም ተከትሎ ንጉሱ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ውሳኔውን ተቀበለው ቢያጸድቁም ከአስር ዓመት በኋላ ሥምምነቱን ወደ ጎን በመተው ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር ቀላቀለዋታል። ይህም በወቅቱ የነበረውን የኤርትራ ወጣት ያስቆጣ በመሆኑ ኩነቱን ተቃውመው ነጻ ኤርትራን እውን ለማድረግ ትግል ማድረግ መጀመራቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። የተጀመረው ንቅናቄ ለሰላሳ ዓመታት ያክል ቆይቶ፤ የወታደራዊ መንግሥት በኃይል ከተገረሰሰ በኋላ እ.ኤ.አ 1993 ኤርትራ በሕዝበ ውሳኔ ሉአላዊ አገር ለመሆን በቃች። ከአምስት ዓመት በኋላም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የድንበር ውዝግብ ተከስቶ ወደ ጦርነት በማምራት በሁለቱም ወገን 80 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል። ይህንንም ውጥረት ለማርገብ በወቅቱ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የአልጀርሱን ስምምነት በሦስተኛ ወገን አደራዳሪነት ተፈራርመዋል። ይሁንና ስምምነቱ በሁለቱ ወገኖች ገቢራዊ ባለመደረጉ አገሮቹ ሰላማዊ የሚባል ግንኙነት ርቋቸው እርስ በእርስ ሲወነጃጀሉ መቆየታቸው የሚታወስ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በኤርትራ ላይ ከሽብርተኝነትና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ማዕቀብ ጥሎባት ቆይቷል። ይህም አገሪቱን ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አግልሏታል። ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መጋቢት ላይ ወደ ሥልጣን  ሲመጡ ከኤርትራ ጋር ሰላም ለመፍጠር እንደሚሰሩ በገለጹት መሰረት ለኤርትራ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት ሰላማዊ የሆነ ግንኙነት ለመፍጠር ችለዋል። በተለይም የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ ም የአልጀርሱን ሥምምነት ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያ እንደምትቀበል ያሳለፈው ውሳኔ ኢትዮጵያ ለሰላም ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ ነበር። ይህንንም ተከትሎ የኤርትራው ፕሬዝዳንት የልዑክ ቡድን ወደ አዲስ አበባ በመላክ አገራቱ ሰላማቸውን ዳግም ወደ ነበረበት ማስመለስ ችለዋል። በመቀጠልም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ ም ወደ አስመራ አቅንተዋል፤ ዛሬ ደግሞ ፕሬዝዳንት ኢሳያሰ አፈወርቂ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ ገብተዋል። መሪዎቹም ዳግም የተሟላ ግንኙነትን በመመሥረት ለ20 ዓመታት የዘለቀውን የሁለቱ አገሮች አለመግባባት በመቋጨት አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም