የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ህለፈት የተሰማውን ሀዘን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ህለፈት የተሰማውን ሀዘን ገለጸ
አዲስ አበባ፣መስከረም 20/2013(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ህለፈት የተሰማውን ሀዘን ገለጸ።
ፕሮፈሰር መስፍን አንጋፋ ምሁር፣ ታሪክ አዋቂና ፖለቲከኛ ከመሆናቸው ባለፈ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጀግና ተብለው የሚታወሱ መሆናቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።
ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳለው ፕሮፌሰር መስፍን ከታላላቅ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች አንዱና ታሪክ የሚያስታውሳቸው ምሁር ነበሩ ብሏል።
ለሰብዓዊ መብት መከበር የማይናወጥ ቁርጠኛ አቋም የነበራቸው፤ በዚሁ አቋማቸው ለበርካታ ጊዜ ለእስር የተዳረጉ እንደነበሩም አስታውሷል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት መስራች አባልም መሆናቸውን ጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ "ፕሮፌሰር መስፍን አንጋፋ ምሁር፣ መምህር፣ የታሪክ አዋቂና ብቁ ፖለቲከኛ ነበሩ" ሲሉ ገልጸዋቸዋል።
ለፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ቤተሰቦችና ወዳጆች በኮሚሽኑ ስም መፅናናትን ተመኝተዋል።