የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የዓመቱ ምርጥ የአፍሪካ ገንዘብ ሚኒስትር ሽልማትን ተቀበሉ - ኢዜአ አማርኛ
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ የዓመቱ ምርጥ የአፍሪካ ገንዘብ ሚኒስትር ሽልማትን ተቀበሉ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 20/2013 (ኢዜአ) የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ምርጥ የ2020 የአፍሪካ ገንዘብ ሚኒስትር ሽልማትን ተቀበሉ፡፡
ሚኒስትሩ ሽልማቱን የተቀበሉት በ5ኛው የአሜሪካ-አፍሪካ ኢንቨስትመንት የፖሊሲ ውይይት በተካሄደ መድረክ ነው።
ሽልማቱ እ.አ.አ በጥቅምት 2018 በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የገንዘብ ሚኒስትር ሆነው እንዲያገለግሉ የተሰጣቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ባሳዩት ቆራጥ የስራ አመራርና በተለይም በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ ጥልቅ የኢኮኖሚ ሪፎርሞችን በመምራት ነው ተብሏል።
በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በሳል አመራር በመስጠት፣ ከልማት አጋሮች የውጭ ሀብት ፍሰት እንዲጨምር በማደረግና የአገሪቷ የብድር አስተዳደር በአግባቡ እንዲመራ ማስቻላቸው ሚኒስትሩን ለሽልማቱ ካበቋቸው መካከል ተጠቅሰዋል።
ከአበዳሪ አገራትና ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የብድር መክፈያ ጊዜ እንዲራዘም በማድረግ የነበራቸው ጉልህ ድርሻም እንዲሁ።
ኢትዮጵያ ከምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር ያላት ኢኮኖሚያዊ ትብብር እንዲጠናከር ከፍተኛ ሚና እንደነበራቸውም በሽልማት ሥነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ በዓለምና በአገር አቀፍ ደረጃ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በተከሰተበት ጊዜ ጉዳቱን ለመቋቋም የሚያስችሉ የገንዘብና የፖሊሲ ውሳኔዎችን በማራመድ ከፍተኛ ተጽዕኖ ላደረባቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ችለዋል ተብሏል።
እነዚህ ውሳኔዎች ወረርሽኙ ሊያስከትል የሚችለውን ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ በመታደግ ወሳኝ አስተዋፅኦ እንደነበራቸውም ተጠቅሷል።
ሚኒስትሩ ሽልማቱን ከተቀበሉ በኋላ ባደረጉት ንግግር "2020 ለሁላችን አስቸጋሪ ዓመት ነበረ፤ በዓለማችን ታይቶ የማይታወቅ ወረርሽኝ ተከስቶ በርካታ ተግዳሮቶች እንደፈጠረ በማስታወስ ሕይወት ለማዳን ብሎም ፈጣን ኢኮኖሚዊ እድገት ለማስቀጠል ትልቅ ፈተና ገጥሞናል" ብለዋል።
በዚህ ፈታኝ ወቅት ይህ ሽልማት መገኘቱ በኢትዮጵያ መንግስት ተግዳሮቶቹን ለመወጣት ላደረገው ጥረት እውቅና እንደሚሰጥ አቶ አህመድ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ባለፉት አስርታት በመሰረተ ልማትና በሰው ሃብት ከፍተኛ መሻሻል የታየ ቢሆንም የግሉ ዘርፍ ሚና በሚፈለገው ደረጃ ላይ ባለመድረሱ ይህንን የልማት አጋር ለማጎልበት ወደ ዘላቂ የልማት ጎዳና የሚወስዱ ፕሮግራሞች እንደተቀየሱም ገልጸዋል።
"ይህ የጀመርነው መንገድ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በድህነት ቅነሳና ሁሉን አቀፍ የዕድገት መንገድ ለማስቀጠል ያመቻቻል የሚል እምነት አለን" ብለዋል።
በአሜሪካ-አፍሪካ ኢንቨስትመንት ፎረም የፖሊሲ አውጪዎችን፣ የግሉ ሴክተር መሪዎችን፣ የኢንዱስትሪ አካላትን፣ ሲቪል ማህበራትና በአሜሪካ-አፍሪካ የሚገኙ ባለድርሻ አካላትን በማሰባሰብና የወደፊት ግንኙነቶችን በሚያግዙ የፖሊሲ አቅጣጫዎች የልምድ ልውውጦች ተደርገዋል።
በመድረኩ ላይ የአሜሪካ-አፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ትብብርና የኢንቨስትመንት ዕድሎች ላይ ምክክርም ተካሂዷል።
እንዲሁም በመድረኩ ላይ በአሜሪካ-አፍሪካ ግንኙነቶች ውስጥ እንደ ስደተኞች ፍልሰት፣ የወጣት ሥራ አጥነትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ባሉ ጉዳዮችም ውይይቶች ተካሂደዋል።
በተጨማሪም መድረኩ እ.አ.አ. በ2020 በአፍሪካ የንግድ ሥራ አመራር የላቀ ውጤት ላስመዘገቡም ሽልማት ተበርክቷል።
የስዋዚላድ ጠቅላይ ሚኒስትር አምብሮስ ማንዱሎ ድላሚኒ፣ የቀደሞ የሴራሊዮን ፕሬዚዳንት ኤርነስት ባይ ኮሮማ፣ የቀድሞ የላይቤሪያ የገንዘብና ልማት ዕቅድ ሚኒስትር ሳሙኤል ትዌህ፣ የኬንያው የናኩሩ ገዥ ሊ ኪያንያንጁ እና የጋና ባንክ ገዥ ዶክተር ኤርነስት አዲሰን በመድረኩ ተሳትፈዋል።