የምርት ገበያን በማዘመን ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ

17

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20/2013 (ኢዜአ) የምርት ገበያን በማዘመን ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማሳደግ እንደሚገባ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የምርት ገበያን ለማዘመን እየተሰሩ ባሉ የማሻሻያ ሥራዎች ላይ ከተጠሪ ተቋማትና ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ውይይት አድርጓል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚንስትሩ አቶ መላኩ አለበል በውይይቱ ላይ እንደተናገሩት የምርት ገበያን በማዘመን የውጭ ምንዛሬን ማሳደግ ያስፈልጋል።

ለአገሪቱ ጤናማ የኢኮኖሚ እድገት የወጪ ንግዱን ማስፋፋት እና ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማሳደግ ወሳኝ ሥራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ለዚህም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የምርት ብክነትን መቀነስ እና ለዓለም አቀፍ ገበያ በሚፈልገው መጠን እና ጥራት መቅረቡን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ባህላዊውን የግብርና ምርቶች የግብይት አካሄድ በመቀየር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማሻሻል እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

"ምርት ገበያው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ምርቶች የሚገበያዩበት በመሆኑ ለኢኮኖሚያችን እድገት የማይተካ ቁልፍ አስተዋጽኦ አለው" ብለዋል ሚኒስትሩ ።

ለዚህም ባለፉት12 ዓመታት ምርት ገበያ ባደራጀው መሰረተ ልማትና የአገልግሎት አሰጣጥ ስርአት 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ምርት በ274 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ለማገበያየት መቻሉን አንስተዋል።

አቶ መላኩ እንዳሉት ዘመናዊ የግብይት ስርአት ባለው ልዩ ባህሪና ተለዋዋጭነት ምክንያት በየጊዜው የአሰራር ማሻሻያና የተጠቃሚዎችን እውቀት ማሳደግ ይፈልጋል።

በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የመጋዘን ኦፕሬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ  በኃይሉ ንጉሴ   በምርት ግብይት ላይ በ2012 የተሰሩ ማሻሻያዎችን አቅርበዋል።

በዚህም በ23 ቅርንጫፎች የምርት ደረጃ የማውጣት፣ የማከማቸት እና የማስረከብ አገልግሎት መስጠት እንደተቻለ ነው የገለጹት

የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ የግብርና ምርቶችም ወደ ግብይት ስርአት መግባታቸውን ጠቁመዋል።

"ለቡና አቅራቢ እና ላኪ ሕብረት ሥራ ማህበራት የልዩ መስኮት ግብይት በማዘጋጀት ድርድርን መፍጠር የሚችሉ ተገበያዮችን በማስገባት ሚዛናዊነት መፈጠር ተችሏል" ብለዋል።

ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶች ለኮንትሮባንድ ንግድ እንዳይጋለጡ ጠንካራ የክትትል ስርአት መዘርጋቱንም ኃላፊው ገልጸዋል።

እንደእሳቸው ገለጻ በተያዘው የ2013 ዓመትም አዳዲስ ምርቶች ወደ ግብይት ስርአቱ እንዲገቡ ይደረጋል።

በተለያዩ አካባቢዎች መጋዘኖች እንዲሁም አዳዲስ የጥራጥሬ እና የቅባት እህሎች መቀበያዎች ይገነባሉ።

"በተመረጡ ቅርንጫፎችም ዲጂታል ሚዛን በማስገጠም የሚፈጠሩ የምርት ጉድለቶችን ለማረም ይሰራልም" ብለዋል።

ማዕድናትና ሌሎች የኢንዱስትሪ ምርቶችን በቀጣይ ወደግብይት ስርአት ማስገባት፣ የግብይት ስርአቱ ተሳታፊዎች ባሉበት ሆነው መገበያየት የሚችሉበትን የግብይት ስርአት መዘርጋት እና የአቅም ግንባታ ሥራዎች ለቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም