ከአምስት ዓመት በኋላ ሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የኃይል ተጠቃሚ ይሆናሉ ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ከአምስት ዓመት በኋላ ሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የኃይል ተጠቃሚ ይሆናሉ ተባለ
አዲስ አበባ መስከረም 20/2013 (ኢዜአ) ከአምስት ዓመት በኋላ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የኃይል አቅርቦት ተደራሽ ማድርግ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ በዝግጅት ላይ እንደሆነ ተገለጸ።
በውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አዘጋጅነት 'የኤሌክትርክ ዘርፍ ሪፎርም ፍኖተ ካርታ' ላይ ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱ ላይ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጀነር ስለሺ በቀለ እንዳሉት ኢትዮጵያ በኃይል ዘርፍ ልማት እጅግ ኋላ የቀረች አገር ናት።
"ከ110 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አገር በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ ከ4 ሺህ 5 ሜጋ ዋት የማይበልጥ ኃይል እያመረተች ትገኛለች" ብለዋል።
ከአፍርካ አገራት ጋር ስትነጻጸር እጅግ ኋላ የቀረችና 60 ሚሊዮን ሕዝቧ ዘመናዊ የኃይል አቅርቦት ተጠቃሚ እንዳልሆነም ይገልጻሉ።
በዝግጅት ላይ የሚገኘው ፍኖተ ካርታ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ሁሉም የአገሪቷ ሕዝብ ኃይል እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑንም ነው ኢንጀነር ስለሺ የገለጹት።
"በፍኖተ ካርታው ትኩርት ከተሰጣቸው መካከል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያለበት እዳ እንዲቃለል መንገዶችን ማመቻቸት አንዱ ነው" ብለዋል።
በዚህም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ካለበት 370 ቢሊዮን ብር በላይ ዕዳ ግማሹ በገንዘብ ሚኒስቴር ስር አዲስ ለሚቋቋመው የንብረትና የዕዳ ማኔጅመንት ኩባንያ እንዲተላለፍ መወሰኑን አስረድተዋል።
"ይህ መንገድ ዘርፉ በተሻለ መልኩ ከችግር ወጥቶ ለኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ስኬት እንዲንቀሳቀስ ያስችለዋል" ብለዋል።
በተጨማሪም ፍኖተ ካርታው የታሪፍ ማስተካከያ ጥናት፣የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ የመንግስትና የግል አጋርነት ጥናት እንዲሁም የዘርፉን አደረጃጃት ማሻሻያ ጥናት ማካተቱን አመልክተዋል።
በተጨማሪም ጥራትና ወጥነት ያለው አገልግሎት መስጠት፣ የተሻለ የፋይናንስ ስርዓት መዘርጋትና የድርጅቱን ወጪና ገቢ ማጣጣም በፍኖተ ካርታው የተካተቱ መሆናቸውንም ነው የጠቆሙት።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥር አስፈጻሚ አቶ ሽፈራ ተሊላ "በ'ብርሃን ለሁሉም' መርሃ ግብር ዕቅዱ የሚሳካ ይሆናል" ብለዋል።
በዚህም የኃይል አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ፣ ከተለያዩ ዘርፎች ኃይል ማመንጨት መቻልና ኃይል ለሌሎች አገራት መላክ የዕቅዱ አካል መሆኑን አብራርተዋል።
"ከዚህ ባለፈም ድርጅቱ በፋይናንስ ረገድ ጠንካራ እንዲሆንና የግል ዘርፉን በስፋት የማሳተፍ ሥራ የሚሰራ ይሆናል" ነው ያሉት።
እንደሥራ አስፈጻሚው ገለጻ በአሁኑ ወቅት ከሌሎች አገራት አንጻር ሲታይ ርካሽ የሆነውን የኃይል ታሪፍ ተመጣጣኝ በማድርግ ገቢ የማሳደግ ሥራ ይሰራል ነው ያሉት።
የአገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችን የኃይል ተጠቃሚ በማድረግ በኩል 1 ሺህ 300 ትምህርት ቤቶችን እና 2 ሺህ 700 ጤና ጣቢያዎችን የኃይል የጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱንም ገልጸዋል።
አቶ ሽፈራ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ሁሉንም የአገሪቷን ሕዝቦች የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ 6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገ ገልጸው፣ ይህም ከህዝብ፣ ከመንግስትና ከለጋሽ አካላት የሚገኝ መሆኑን አመልክተዋል።