ቀጥታ፡

ማኅበሩ በጎርፍ አደጋ ለተጎዱ ዜጎች በተለያዩ ጊዜያት የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በጎርፍ አደጋ ለተጎዱ ዜጎች በተለያዩ ጊዜያት ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።

በኢትዮጵያ በክረምት ወራት የጣለውን ከፍተኛ ዝናብ ተከትሎ የተከሰተው የጎርፍ አደጋ ከወትሮው በተለየ በርካታ ዜጎች ላይ ጉዳት አስከትሏል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ምክትል ዋና ፀሐፊ አቶ እንግዳ ማንደፍሮ የጎርፍ አደጋ በአፋር ክልል ያስከተለው ጉዳት የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ጋምቤላ ክልሎች በርካታ ዜጎች በጎርፍ አደጋ መጎዳታቸውንም ተናግረዋል።

የጎርፍ አደጋዎች መከሰት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ማኅበሩ በሦስት ዙር የተለያዩ ድጋፎችን ለተፈናቃዮች ማድረጉን ገልጸዋል።

በምግብ ድጋፉ ለጎርፍ ተጎጂዎች ዱቄት፣ ፓስታ፣ ማካሮኒና ዘይት መሠጠቱን ተናገረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ምግብ ነክ ባልሆኑ ድጋፎች ከአልባሳት በተጨማሪ የሴቶች ንጽሕና መጠበቂያና ሌሎች አስፈላጊ ቁሶችን ድጋፍ ለማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።

ማኅበሩ ከነሐሴ ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት ላደረጋቸው ድጋፎች እስካሁን ድረስ ከስድስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንም አስታውቀዋል።

በቀጣይ በተለያዩ አካባቢዎች ለጎርፍ ተጎጂዎች ማኅበሩ የሚያደርገውን ድጋፍ  እንደሚቀጥል የገለጹት አቶ እንግዳ፣ በአራተኛ ዙር የድጋፍ ሥራው  ተጨማሪ እገዛ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

"በአሁኑ ወቅት ክረምቱ እየወጣ መሆኑን ተከትሎ የጎርፍ አደጋ ቢቀንስም ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉና በንብረታቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ስዎችን ለማቋቋም በሚሠራው ሥራም ማኅበሩ የራሱን አስተዋጽኦ ያደረጋል" ብለዋል።

በ2012 የክረምት ወራት በተለያዩ አካባቢዎች የጣለው ከፍተኛ ዝናብ ያስከተለው የጎርፍ አደጋ በማሣቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸው በርካታ ዜጎች ያሉ ሲሆን ቁጥራቸው 300 ሺህ ያህል ሰዎችም ከቄያቸው መፈናቀላቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምከንያት ለችግር የተጋለጡ ስዎች ሰብአዊ ድጋፍ በማድረግ የሚታወቅ ሲሆን በኢትዮጵያ ከተመሠረተ 85 ዓመታትን አስቆጥሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም