ፖሊስ የሚሰጠውን መመሪያ በብቃት ለመፈጸም በቂ ዝግጅት አድርጓል - ኮሚሽነር እንዳሻው ጣሰው - ኢዜአ አማርኛ
ፖሊስ የሚሰጠውን መመሪያ በብቃት ለመፈጸም በቂ ዝግጅት አድርጓል - ኮሚሽነር እንዳሻው ጣሰው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 20/2012 (ኢዜአ) ፖሊስ እንደሁልጊዜው የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና የሚሰጠውን መመሪያ ተቀብሎ በብቃት ለመፈጸም በሚያስችል መልኩ በቂ ዝግጅት ማድረጉን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽ ኮሚሽነር ጀነራል እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።
ኮሚሽነሩ ይህንን የገለጹት ''ከራስ በላይ ለሕዝብና ለሀገር'' በሚል መሪ ቃል ዛሬ በመስቀል አደባባይ በተካሄደ የፖሊስ ትርዒት ላይ ነው።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ፣ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና አምባሳደሮች ታድመዋል።
በሥነ ሥርዓቱም ላይ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የፌዴራል ፖሊስ አባላት በደህንነትና በፀጥታ ዙሪያ የሚያደርጉትን የመከላከልና የመጠበቅ ተግባር አስመልክተው የተለያዩ ትርዒቶችን አቅርበዋል።
በዓሉን በመክፈቻ ንግግር ያስጀመሩት ኮሚሽነር እንዳሻው ጣሰው የፌዴራል ፖሊስ እንደሁልጊዜው ሁሉ የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና የሚሰጠውን መመሪያ ተቀብሎ በብቃት ለመፈጸም በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በሕዝቦች መካከል ያለውን ሰላምና አንድነት ለመናድ የሀሰትና የሽብር ወሬዎችን በመንዛትና ጊዜንና ወቅትን በመለየት ለረብሽና ለብጥብጥ የሚጋብዙ ቡድኖችና አካላት እንዳሉም አንስተዋል።
ኅብረተሰቡ መሠረተ ቢስ በሆኑ አሉባልታዎች ተነሳስቶ በእኩይ ተግባር እንዳይሳተፍና ለግጭት እንዳይዳረግም ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።
እንደ ኮሚሽነር ጀነራል እንዳሻው ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅትም ሆነ በማንኛውም ጊዜ የአገር ሰላምና የዜጎችን ደህንነት ሥጋት ውስጥ የሚከቱ ድርጊቶችንና አካላትን ለመመከት ኮሚሽኑ ነቅቶ እየሠራ ይገኛል።
በተለይ ጥናትን መሠረት ያደረጉ የሪፎርም ሥራዎች በኮሚሽኑ የተሠሩ መሆናቸውን ገልጸው፤ በዚህም ዘመናዊ፣ በዕውቀትና በብቃት የጎለበቱ የፖሊስ አባላትን ማፍራት እንደተቻለ አስረድተዋል።
ኮሚሽኑ በመረጃ ልውውጥና በግብአት እጅግ ዘመናዊ አሠራርን እየተከተለ መሆኑን በመጠቆም በአሁኑ ወቅት አገሪቷንና ሕዝቧን የሚመጥን የፖሊስ ኃይል መኖሩን አመልክተዋል።
በተለያዩ ጊዜያት በሚከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ የፖሊስ አባላት አካላቸውንና ሕይወታቸውን በማጣት ጭምር ኅብረተሰቡን እየታደጉ መሆናቸውን አስታውሰው፣ በቀጣይም ሕዝብና አገርን የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን በሚገባ እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
ኮሚሽነር ጀነራል እንዳሻው ሕዝቡ ከፀጥታ አካላት ጎን በመሆን ለሰላሙ የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፈዋል።