የወገን ለወገን የቶምቦላ ሎቶሪ ዕጣ ወጣ

71

አዲስ አበባ  መስከረም 19/2013 ( ኢዜአ) የወገን ለወገን የቶምቦላ ሎቶሪ ዕጣ ዛሬ በብሔራዊ ሎቶሪ አዳራሽ ወጥቷል። 

ቶምቦላ ሎተሪው በ2010 ዓ.ም በፀጥታ ችግር ምክንያት ከሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም በኦሮሚያ ልማት ማህበር የተዘጋጀ ነው።

በግንቦት 2010 ዓ.ም ይፋ የተደረገውን ሎተሪ በስድስት ወራት ሸጦ ለማጠናቀቅ ነበር የታሰበው።

ያም ሆኖ ከሁለት ዓመታት በላይ ዘግይቶ ዛሬ መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም መውጣት ችሏል።

የወገን ለወገን የ/ለሚቱ ለሚፍ/ ቶምቦላ ሎቶሪ ሃሳብ አመንጪና የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሞቲ ሞረዳ እንደገለጹት ለሎቶሪው በተለመደው መልኩ ሽያጭ እንዳልተካሄደ ጠቁመዋል።

በአንፃሩ በባለሀብቶች፣ በመንግስት የስራ ኃላፊዎችና በተለያዩ ሚኒስትሮች አማካኝነት ሽያጩ መካሄዱን ገልጸዋል።

ሎቶሪው ጊዜዉን ጠብቆ እንዳልወጣ የገለጹት አቶ ሞቲ ምክንያቱ ደግሞ በአገሪቷ የነበረው የፖለቲካ ሁኔታ ነው ብለዋል።

ከተሰራጨው 39 ሚሊዮን የሎተሪ ትኬት የተሸጠው 12 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሲሆን ይህም 30 በመቶው ነው ብለዋል።

12 ሚሊዮን 79 ሺህ 331 ሎተሪ ተሸጦ 241 ሚሊዮን 586 ሺህ 620 ብር ገቢ መገኘቱንም ገልጸዋል።

በሎቶሪው ዕጣ 447 ሰዎች ዕድለኞች እንደሆኑም ተናግረዋል።

ከወጡት ዕጣዎች መካከል በአይነት የመኖሪያ ቤት፣ ገልባጭ ሲኖትራክ፣ ሚኒባስ፣ ባለሶስት እግር ተሸከርካሪ ባጃጅ፣ ላፕቶፕ፣ ስማርት ፎን የሞባይል ስልክና ፍሪጅ ይገኙበታል።

ዛሬ በወጣው ዕጣ መሰረትም ሽልማቶቹ ለዕድለኞች ይሰጣሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም