የኮሮና ቫይረስ ውጤትን በደቂቃዎች የሚመረምር መሳሪያ ስራ ላይ ሊውል ነው

71

  አዲስ አበባ  መስከረም 19/2013 ( ኢዜአ) በአነስተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት የመርመር አቅምን የሚያሳድግና የኮሮና ቫይረስ ውጤትን በደቂቃዎች ውስጥ የሚሰጥ መመርመሪያ መሳሪያ ስራ ላይ ሊውል መሆኑን የአለም የጤና ድርጅት አስታወቀ።

ቢ ቢ ሲ እንደዘገበው አምስት ዶላር ዋጋ ያለው መመርመሪያ መሳሪያ መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት የኮቪድ 19 በሽታ ስርጭትን ለመከላከል የሚከናወነውን ስራ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ነው።

ምርመራዎች ከተደረጉ በኋላ ውጤት እስኪደርስ የሚፈጠረው ክፍተት በርካታ አገራት የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚያደርጉትን ጥረት ወደ ኋላ መጎተቱም ተጠቁሟል። የአለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራል ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም እንደገለጹት፤ ለአጠቃቀም ምቹና ቀላል የሆነው አዲሱ መሳሪያ የምርመራ ውጤት ከ15 እስከ 30 ደቂቃዎች ውስጥ የሚያደርስ ነው።

የቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ከአምራቾች ጋር ባደረጉት ስምምነትም በስድስት ወራት ውስጥ 120 ሚሊዬን መሳሪያዎችን እንደሚያቀርቡም ተናግረዋል። በስምምነቱ ተጠቃሚ የሚሆኑት 133 አገራት ሲሆኑ አብዛኛዎቹም የላቲን አሜሪካ አገራት መሆናቸው ተጠቅሷል።

ይህም የቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ በሆነባቸው አገራት የመርመር አቅማቸውን በማሳደጉ በኩል መሰረታዊ እገዛ እንደሚኖረው ዶክተር ቴድሮስ ገልጸዋል።በተለይም ወደ አካባቢያቸው ለመድረስ ሩቅ በሆኑ ስፍራዎች፣ የቤተ ሙከራ መሰረተ ልማቶች ባልተስፋፋባቸውና በቂ የሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች በማይገኙበት አካባቢዎች ምርመራን ለማስፋፋት ያስችላል ብለዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም