ቀጥታ፡

"ነጋሪ" መፅሄት በአዲሱ ዓመት በርካታ ወቅታዊና አበይት አገራዊ ጉዳዮችን ይዞ ብቅ ብላለች

  አዲስ አበባ  መስከረም 18/2012 ( ኢዜአ)በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በየሁለት ወሩ የምትታተመው "ነጋሪ" መጽሔት ሰፋ ያሉ ወቅታዊና አበይት አገራዊ ጉዳዮችን ይዛ ብቅ ብላለች፡፡

በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት እንዲፋጠን የህግ ልዕልና ወሳኝ መሆኑን መፅሄቱ በስፋት ዳስሷል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሸኝን ለመከላከል የሚከናወኑት የተጠናከሩ ተግባራትም ተቃኝተዋል።

ከኮቪድ ጋር በተያያዘ የተቋረጠውን ትምህርትና የኪነ ጥበብ ዘርፍ አስመልክቶ ባለሙያዎችና ተማሪዎች አስተያየታቸውን አካፍለውናል፡፡

ወረርሽኙን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የኪነጥበብ ባለሙያዎች ተግባር የማይናቅ እገዛ ማበርከታቸውም በስፋት ተዳሷል፡፡

ከዚህ ባለፈ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት በመዘናጋት ወደ ኋላ እንዳይመለስ የጤና ሚኒስቴርና የተለያዩ ባለሙያዎች የሰጡት ምክር ለንባብ በቅቷል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ውሃ ሙሌትና ቀጣይ ስራዎችን በተመለከተም በመፅሄቱ ሰፋ ያለ ዘገባ ተካቷል።

የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴዎች አጠቃላይ ክንውን የተካተተ ሲሆን ህዝቦች በዘመን ሂደት የገነቧቸው በጋራ ማንነትና ባህል ላይ የተመሰረቱ እሴቶች ለምን ተሸረሸሩ ብሎ በመጠየቅም ሰፊ ማብራሪያ ተካትቷል።

በጤናው ዘርፍ የብዙዎችን ልጅ የማግኘት ጉጉት የገደበውን መካንነት መንስዔና መፍትሄዎችን በተመለከተም በዘርፉ የህክምና ባለሙያዎች የተሰጠው ማብራሪያ በእትሙ ተካቶ ለአንባቢያን ቀርቧል፡፡

በኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም የተከናወኑ አበይት ተግባራትና የአዲሱ ዓመት ተስፋዎች በተመለከተም በነጋሪ መጽሔት የተቃኘ በመሆኑ ታነቡ ዘንድ ተጋብዛችኋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም