የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ደጋፊዎች በአፋር ክልል በጎርፍ ለተጉዱ ዜጎች ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ደጋፊዎች በአፋር ክልል በጎርፍ ለተጉዱ ዜጎች ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ መስከረም 18/2012 ( ኢዜአ) የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ደጋፊዎች በአፋር ክልል በጎርፍ ለተጎዱ ዜጎች የምግብ፣ የንጽህና መጠበቂያና የሌሎች ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ ፡፡
የደጋፊዎቹ ተወካዮች ዛሬ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ምክትል ዋና ጸሃፊ በተገኙበት ድጋፉን አስረክበዋል።
የስፖርት ማኅበሩን ደጋፊዎች በመወከል መልዕክት ያስተላለፈው ወጣት ያሬድ መላኩ የክለቡ ደጋፊዎች ከዚህ ቀደምም በተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባራት ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጿል።
በአፋር ክልል በጎርፍ አደጋ ለተጎዱ ዜጎች የተደረገው ድጋፍ የመጀመሪያ እንጂ በዚህ የሚቆም እንዳልሆነም ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅህበር ምክትል ዋና ጸሃፊ አቶ እንግዳ ማንደፍሮ በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው የጎርፍ አደጋ ያስከተለው ችግር ቀላል እንዳልሆነ ጠቁመዋል።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ደጋፊዎች ችግሩን በመረዳት የወገኖቻችን ችግር የእኛም ችግር ነው በማለት ላደረጉት ድጋፍም አመስግነዋል።
ደጋፊዎቹ ያበረከቱት ድጋፍ ከ200 ሺህ ብር በላይ ግምት እንዳለው ተገልጿል።