ቀጥታ፡

አልፎ አልፎ ችግሮች ቢገጥሙንም ያለንበት ጊዜ ትልቅ ተስፋን የሰነቀ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 18/2013 (ኢዜአ) "አልፎ አልፎ ችግሮች ቢገጥሙንም ያለንበት ጊዜ ትልቅ ተስፋን የሰነቀ ነው" ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዛሬው እለት ከእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባላት ጋር ውይይት አድርገዋል።በውይይቱም ኢትዮጵያ አሁን ላይ በርካታ ተስፋዎችን ሰንቃለች ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዳሴ ግድብ ውጤታማ ክንውን፣ በኮሮና ቫይረስ እየተፈተነም ቢሆን የአገሪቱ ኢኮኖሚ ማደጉ ትልቅ ተስፋ መሆኑን ገልጸዋል።

በእነዚህ ውጤታማ እንቅስቃሴዎች እየተጓዝን ቢሆንም አልፎ አልፎ ችግሮች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።

ሆኖም እነዚህ ችግሮች የኢትዮጵያ ለማሳካት የጀመረቻቸውን ታላላቅ ትልሞች አያደናቅፉም ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አስካሁን ያደረጋቸውን ጥረቶች በማድነቅ በቀጣይ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ ለመሆን እንዲሰራም ጠይቀዋል።

መንግስትም የኮሚሽኑን መልካም ጅምሮች ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመው፤ ኮሚሽኑም ያለውን አቅም ለማብዛት ከተለያዩ ተቋማት ጋር ተቀራርቦ እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሴ ኮሚሽኑ እስካሁን ስላከናወናቸው ተግባራት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ሂደት ስትራቴጂክ አቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን አምስት የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎችን ማደራጀቱንም ገልጸዋል።ከቋሚ ኮሚቴው መካከል ሶስቱ የኮሚሽኑን ዋና ዋና ተግባራት የሚያከናውኑ መሆናቸውንም አብራርተዋል።በዚህ ዓመት በአገሪቱ 11 የተለያዩ አካባቢዎች ኮሚሽኑ ቅርንጫፍ ዕህፈት ቤት ለመክፈት መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም