ለገነባናቸው ቤቶች ኤሌክትሪክ ለማስገባት ክፍያ ብንፈጽምም አገልግሎቱን ልናገኝ አልቻልንም - ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለገነባናቸው ቤቶች ኤሌክትሪክ ለማስገባት ክፍያ ብንፈጽምም አገልግሎቱን ልናገኝ አልቻልንም - ነዋሪዎች
ደብረ ማርቆስ መስከረም 18/2013 ( ኢዜአ ) በማህበር ተደራጅተን ለገነባናው መኖሪያ ቤቶች ኤሌክትሪክ ለማስገባት ክፍያ ብንፈጽምም አገልግሎቱን ሳናገኝ ሁለት አመት ሆኖናል ሲሉ የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ።
በከተማው በማህበር የተደራጁ 160 ነዋሪዎች ለገነቧቸው የመኖሪያ ቤቶች ኤሌክትሪክ ለማስገባት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ቢከፍሉም አገልሎቱን ባለማግኘታቸው ቅሬታቸውን በተወካዮቻቸው አማካኝነት ገልጸዋል ።
የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ ታምር ተሰራ ለኢዜአ እንደገለጹት የማህበሩ አባላት በከተማው ቀበሌ 07 ባታ ሳይት ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በተሰጣቸው ቦታ ላይ 160 ቤቶችን ገንበተው መኖር ጀምረዋል ።
ለተገነቡት ቤቶች ኤሌክትሪክ ለማስገባት 2011 ዓም ከአባላቱ የተሰበሰበ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ለአማራ ክልል ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ደብረማርቆስ ዲስትሪክት ክፍያ መፈጸሙን አስታውሰዋል ።
"ዲስትሪክቱ የትራንስፎርመር ተከላና የመስመር ዝርጋታ ካጠናቀቀ በኋላ የመብረቅ መከላከያ መሳሪያ አልተገኘም በሚል የኤሌክትሪክ ኃይሉን ወደ መኖሪያ ቤቶቹ ሳያደርስ ስራውን አቋርጧል" ብለዋል ።
ከማህበሩ አባላት ተጨማሪ በተሰበሰበ 170 ሺህ ብር የተጠየቀው እቃ ተገዝቶ ስራው እንዲቀጥል ቢደረግም ለቀረበው እቃ ጥራት ማረጋገጥ አልተቻለም በሚል በድጋሚ ስራውን ማቋረጡን ተናግረዋል ።
ለቀረበው እቃ ህጋዊ ደረሰኝና ከኢትዮጵያ ተስማሚነትና ምዘና ድርጅት የጥራት ማረጋገጫ ቢያቀርብም ዲስትሪክቱ ስራውን አቋርጦ በመቅረቱ አገልግሎቱን ማግኘት እንዳልቻሉ አስታውቀዋል ።
የማህበሩ አባልና ተወካይ መሪጌታ ፍስሃ ውዱ በበኩላቸው በማህበር ተደራጅተው በ2007 አም በተሰጣቸው የግንባታ ቦታ በሰሩት ቤት እየኖሩ መሆኑን ተናግረዋል ።
በማህበራቸው በኩል ለቤታቸው ኤሌክትሪክ ለማስገባት ከሁለት ዓመት በፊት በግላቸው ስምንት ሺህ ብር ማዋጣታቸውን አስታውሰዋል ።
ዲስትሪክቱ መስመር ዘርግቶ ትራንስፎርመር ካስቀመጠ በኋላ ስራውን በማቋረጡ አገልግሎቱን ሳያገኙ መቆየታቸውን ተናግረዋል ።
"የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ባለመሆኔ በእለት ተእለት ኑሮየ ላይ ጫና አሳድሮብኛል" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል ።
በተመሳሳይ መልኩ ቅሬታቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው የማህበሩ አባላልና ተወካይ አቶ ደግአረገ ወርቁ ናቸው።
የሚመለከተው አካል የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የደብረማርቆስ ዲስትሪክት ዳይሬክተር አቶ ፈንታሁን ምህረቱ ከተቋሙ የዝቅተኛ መስመር ዝርጋታ የሚሆኑ እቃዎች ባለመኖራቸው ችግሩ መፈጠሩን ተናግረዋል ።
ማህበሩ የሚያስፈልገውን እቃ በግል ለማቅረብ ባቀረበው ጥያቄ መሰረት መፈቀዱን የገለጹት ዳይሬክተሩ "ለቀረበው እቃ ከአማራ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዲዛይንና ኢንጅነሪንግ ዘርፍ ማረጋገጫ እንዲያቀርብ ተጠይቋል " ብለዋል።
"ማህበሩ በግል ገዝቶ ያቀረበውን እቃ ወስዶ በስራ ክፍሉ በኩል እንዲያስፈትሽ ቢጠየቅም ፈቃደኛ ባለመሆኑ ስራውን ማስቀጠል አልተቻለም" ብለዋል።
ማህበሩ በዲስትሪክቱ በኩል በቀረበለት አቅጣጫ መሰረት እቃውን ለአማራ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዲዛይንና ኢንጅነሪንግ ዘርፍ አቅርቦ በማስፈተሽ የጥራት ማረጋገጫ ሲቀርብ ስራው የሚጠናቀቅ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል ።