ቀጥታ፡

በመንገድ ብልሽት ምክንያት መቸገራቸውን ተገልጋዮች እና አሽከርካሪዎች ገለጹ

አሶሳ መስከረም 18/ 2013(ኢዜአ) ፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከአሶሳ ወደ መተከል የሚወስደው መንገድ በመበላሸቱ መቸገራቸውን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተገልጋዮች እና አሽከርካሪዎች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባስልጣን መንገዱን በአስፓልት ኮንክሪት ለማስገንባት እየሰራ  መሆኑን አስታውቋል፡፡

  የአሶሳ ነዋሪው አቶ አበበ ፈቃዱ እንዳሉት ወደ መተከል የሚወስደው መንገድ በመበላሸቱ ለትራንስፖርት አገልግሎት አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡

በዚህም ምክንያት ከአሶሳ በህዳሴው ገድብ በኩል ወደ መተከል ዞን ግልገልበለስ ከተማ የአንድ ቀን ጉዞ በአሁኑ ወቅት ሁለት ቀናትን ይፈጃል ብለዋል፡፡

ይህም ለተጨማሪ ወጪ ከመዳረጉም በላይ በተለይም ህጻናት፣ አረጋዊያን እና ህመምተኞች ላይ እንግልት እንዳስከተለ ተናግረዋል፡፡

በማህበራዊ ግንኙነታቸው ት ላይም ጫና ማሳደሩን ጠቁመዋል፡፡

ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ በህዳሴው ግድብ በከባድ መኪና አሽከርካሪነት እየሠሩ እንደሚገኙ የተናገሩት  አቶ ካሣሁን አራጋው በበኩላቸው  በተለይም ከህዳሴው ግድብ እስከ ማምቡክ ከተማ ያለው መንገድ ብልሽት እየጣለ  ባለው  ዝናብ   ምክንያት ችግሩ መባባሱን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ምክንያት ከህዳሴው ግድብ ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ  ሲሚንቶ ጭነው ደርሶ ለመመለስ የሚፈጅበቻው ጊዜ ከአምስት ወደ ስምንት ቀናት እንደሚፈጅባቸው ጠቅሰዋል፡፡

ተሸከርካሪ እየተበላሸባቸው ለቀናት በየመንገዱ እንደሚቆዩ ጠቅሰው አደጋ የሚከሰትበት አጋጣሚ እንዳለም ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ መንገዶች ባስልጣን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ከአሶሳ መተከል ያለው መንገድ ግንባታ በአራት ተከፍሎ በአስፓልት ኮንክሪት ለማስገንባት ግንባታ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

በአሶሳ በኩል ከሆሞሻ-ሸርቆሌ-ህዳሴ ግድብ ያለው መንገድ በአስፓልት መንገድ ለማስጀመር ጨረታ ወጥቶ አሸናፊውን የመለየት ሥራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

በአብዛኛው ቅሬታ የተነሳበት እና ከባድ ብልሽት የደረሰበት  ከፓዌ መገንጠያ-ማንኩሽ- ህዳሴው ግድብ ያለው 140 ኪሎ ሜትር ከሚጠጋ መንገድ ውስጥ 96 ኪሎ ሜትር አስፓልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ከዓመት በፊት መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡

ሆኖም  ግንባታውን በሚያካሂደው የቻይና ኩባንያ ባጋጠመው የአፈጻጸም ችግር እና የሰው ኃይል እጥረት ሳቢያ የመንገዱ ሥራ መጓተቱን አቶ ሳምሶን ገልጸዋል፡፡

በአካባቢው የሚገኙ ቤቶች እና ሌሎችም ንብረቶችን በወቅቱ አለመነሳታቸውም ለመንገዱ መዘግየት ሌላው ምክንያት እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

ስራውን ለመቀጠል ተቋራጩ  በአሁኑ ወቅት የግንባታ ቁሳቁስ ወደ አካባቢ ማጓጓዝ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

ከፓዌ መገንጠያ እስከ ህዳሴው ግድብ ባለው መንገድ ብቻ የፌደራል መንግስት ሁለት ቢሊዮን 200ሚሊዮን  የሚጠጋ ብር መመደቡን ጠቅሰዋል፡፡

መንገዶቹ በተያዘው የበጀት ዓመት  ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

በመንገዶች ግንባታ መዘግየት ላይ የሚታየውን ችግር ለመፍታት ባለስልጣኑ ክትትል እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው ህብረተሰቡ እና የአካባቢው አስተዳደርም ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ መልዕክታቸውን አሰተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም