ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማኅበር በቦሌ ክፍለ ከተማ ለሚገኙ አረጋዊያን ማዕድ አጋሩ

መስከረም 16/2012 የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማኅበር አባላት ከቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት አስተዳደር ጋር በመተባበር የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ ለ100 አቅመ ደካማ አረጋዊያን ማዕድ አጋርተዋል፡፡ 

ለአረጋዊያኑ አምስት ኪሎ ሽንኩርት፣ ሶስት ሊትር ዘይት፣ አምስት ኪሎ ዱቄት፣ አንድ ኪሎ በርበሬ፣ 10 እንቁላልና ግማሽ ኪሎ አይብ ለእያንዳንዳቸው ተበርክቶላቸዋል።

የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ አየሉ ጎሹ የማኅበሩ አባላት ለአረጋዊያኑ ላበረከቱት አስተዋፅኦ አመስግነዋል።

የማኅበሩ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም ስዩም ድጋፉ በ150 ሺህ ብር ወጪ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።

ማኅበሩ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳቢያ ለችግር የተጋለጡ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለመደገፍ አምስት አባላት ያሉት የድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ተናግረዋል።

የዲያስፖራው ማኅበረሰብ ያለውን እውቀትና አቅም በማስተባበር አገሩን ይደግፋልም ብለዋል።

በውጭና በአገር ውስጥ የሚገኙ የዲያስፖራ ማኅበር አባላትን በማሳተፍ በቀጣይ በሚከበሩ በዓላት በአዲስ አበባና በክልሎችም ከተቸገሩ ዜጎች ለመቆም እንደሚንቀሳቀሱም ተናግረዋል።

የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 አስተዳደር ለወረዳው ነዋሪዎች ድጋፍ ላደረጉ የዲያስፖራ ማህበር አባላት የምስጋና ምስክር ወረቀት አበርክተዋል።

ድጋፍ የተደረገላቸው አረጋዊያንም ደስታቸውን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም