ኢትዮጵያና ቻይና በፖለቲካ መተማመን፣ በትብብር እና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ አጋርነት መስርተዋል--አምባሳደር ታን ጂያን

108

አዲስ አበባ መስከረም 17/2013(ኢዜአ) ኢትዮጵያና ቻይና በፖለቲካ መተማመን፣ በትብብር እና በጋራ ተጠቃማኒነት ላይ ያተኮረ አጋርነት መመስረታቸውን ተሰናባቹ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂያን ተናገሩ፡፡

አገራቱ በሁሉም ዘርፍ ፈጣን ልማት ማስመዝገባቸውን ጠቅሰው በተለይ በቻይና የሮድ ኤንድ ቤልት ኢኒሸቲቭ እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የመሰረቱት አጋርነት የተለየ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

"ኢትዮጵያ ሮድ ኤንድ ቤልት ኢኒሸቲቭን በተመለከተ በአፍሪካ መተኪያ የሌላት የቻይና አጋር ናት፣ በአፍሪካ የሮድ ኤንድ ቤልት ኢኒሸቲቭን ከፈረሙት ቀዳሚ አገራት አንዷም ናት” በማለት አምባሳደሩ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቀዋል፡፡

"ኢትዮጵያ ያለምንም ማንገራገር ኢኒሸቲቩን በንቃት እየደገፈች ነው፤ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ከሁለትዮሽ አጋርነት በእጅጉ የላቀ ስለሆነ በቻይና አፍሪካ እና በደቡብ ደቡብ ግንኙነት ሞዴል የሚሆን ነው” ብለዋል፡፡

ቻይና በኢትዮጵያ ታላቋ የንግድ አጋርና የቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፈሰስ አድራጊ መሆኗን የጠቆሙት አምባሳደሩ፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የኢኮኖሚ ትብብር የቻይና አፍሪካ ፎረምን እና የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሸቲቭን መሰረት በማድረግ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን አመልክተዋል።

ቻይና ለኢትዮጵያ የልማት ግስጋሴ የምታደርገው ድጋፍ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገና ዘርፈ ብዙ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

አምባሳደር ታን እንዳሉት ድጋፉ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የማይጻረርና ኢኮኖሚዋን በማሳደግ የዜጎቿን ኑሮ ለማሻሻል የምታደርገውን ጥረት ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡

"ይህ አቋማችን ፈጽሞ የማይለወጥና በጽኑ መሰረት ላይ የቆመ ነው "ብለዋል፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ "ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ በማደግ ላይ ያለውን የኢትዮጵያንና የቻይናን አጠቃላይና ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ሊገድበው የሚችለው ሰማይ ብቻ ነው" ማለታቸውን አስታውሰዋል፡፡

አምባሳደሩ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ በአገሪቱ የሚታየውን ፈጣን እድገት መታዘባቸውንና በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

"በጋራ ከፍተኛ ስኬት አስመዝግበናል " ሲሉም ነው የገለጹት፡፡

በቻይና ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ውስጥ ሦስት ቁልፍ ሁኔታዎች እንዳሉ ጠቁመው፤ "በመተማመን ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ትብብር፣ የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሸቲቭ አጋርነት እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያለው ህብረት ይጠቀሳሉ" ብለዋል፡፡

"በመተማመን ላይ የተመሰረተው የፖለቲካ ግንኙነት ለሁሉም ዘርፍ ዋና መሰረት ነው፤ ሁለቱ አገራት ተከታታይ የሆነ ትብብር ያላቸው ሲሆን በመንግስታት፣ በገዥ ፓርቲዎች፣ በቲንክ ታንክ ቡድኖች፣ በማህበራዊና ባህላዊ ቡድኖች ልምድ ይለዋወጣሉ” ሲሉም አምባሳደር ታን ጂያን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት ግንባታ ላይ የቻይና ኩባንያዎች በስፋት እየተሳተፉ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም በ10 ሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን የሥራ ዕድል ማስገኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ከሥራ ዕድል ፈጠራው ባለፈ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዕድገት ያበረከቱት እገዛ ከፍተኛ መሆኑንም አምባሳደሩ አንስተዋል፡፡

የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማትንና ሸገርን ማስዋብ ለተሰኘው ፕሮጀክት ቻይና እገዛ እያደረገች መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

"ፕሮጀክቱ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ የላቀ ሚና ያለውና በዘመናዊ መልክ የሚገነባ ሲሆን የነዋሪዎቹን ፍላጎት መሰረት አድርጎ ንድፉ ተሰርቷል፤ ይህም የኢትዮጵያን የቀደመ ስልጣኔ፣ የባህል ስብጥርና አንድነት ያሳያል" ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ለኢትዮጵያ አዲስ ገጽታ ከማላበስ ባለፈ የአገልግሎት ዘርፉን በሚገባ እንደሚያሳድገው፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና የገቢ አቅሟን ከፍ እንደሚያደርገውም እምነቴ የላቀ ነው” ሲሉም አምባሳደሩ አክለው ገልጸዋል፡፡ 

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ምዋዕለንዋያቸውን በስፋት እያፈሰሱ ይገኛሉ።

ባለሀብቶቹ በጨርቃ ጨርቅ፣ በመድኃኒት ማምረቻ፣ በግንባታ መሳሪያዎች፣ በብረታ ብረት፣ በሴራሚክ እና በቀርክሃ ወረቀት ምርት ላይ መሳተፋቸውንም ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በቅርቡ በወጣው መረጃ እስከ ሰኔ 2012 ዓ.ም መጨረሻ 1ሺህ 500 ቀጥተኛ የቻይና ኢንቨስትመንት ወደ ኢትዮጵያ ፈሰስ የተደረገ ሲሆን በገንዘብ ሲለካ 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል ተብሏል፡፡

"ለኢትዮጵያ እድገት የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት፣ ኢንቨስትመንትና መሰረተ ልማት የማይተካ ሚና ያላቸው ሲሆን ዘርፎቹ በኢትዮጵያ በእጅጉ እያደጉና ተደራሽ እየሆኑ ለመምጣታቸው ከልብ የመነጨ ምስክርነቴን እሰጣለሁ" ሲሉም አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም