ቀጥታ፡

የሱዳን ባለሀብቶች ቡድን በቢሾፍቱ ከተማ አቀባበል ተደረገለት

አዲስ አበባ መስከረም 16/2012 (ኢዜአ) ሃያ ሁለት አባላት ያሉት የሱዳን ባለሀብቶች ቡድን ቢሾፍቱ ከተማ ሲገባ በኦሮሚያ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮና በቱሪዝም ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል ተደርጎለታል።

የሱዳን ባለሀብቶች ቡድኑ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮችና የልማት ሥራዎች ለመመልከት መስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱ ይታወቃል።

በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩት የሱዳን ባለሀብቶቹ በኦሮሚያ ክልል በሚኖራቸው ቆይታ የአብያታና ሻላ ሐይቆች፣ የአዋሽና የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርኮች የቱሪዝም መዳረሻዎችን ይጎበኛሉ ተብሏል።

በቢሾፍቱ አካባቢ የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ሀብቶችም ጉብኝት ያደርጋሉ።

የባለሀብቶቹ ቡድን በኦሮሚያ ክልል እስከ መስከረም 21 እንደሚቆይ የተነገረ ሲሆን የክልሉን ቱሪዝም፣ ኢንቨስትመንትና የልማት ሥራዎችን ይመለከታል።

ቡድኑ የመጀመሪያ ጉብኝቱን ያደረገው በአማራ ክልል በሚገኙት በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እንዲሁም የጎርጎራ አካባቢ የቱሪዝም አማራጮችን ነው።

የኦሮሚያ ክልል ጉብኝቱን ሲያጠናቅቅም በደቡብና በአፋር ክልሎች የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን እንደሚጎበኝ ይጠበቃል።

የሱዳን ባለሀብቶች ቡድን የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮች በመቃኘት የልማት ሥራ ጉብኝቱንና የኢትዮጵያ ቆይታውን መስከረም 23 ቀን 2013 ዓ.ም እንደሚያጠናቅቅ ተገልጿል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም