የመስቀል ደመራ በዓል ሃይማኖታዊ ሥነ-ስርዓቱን ጠብቆ ይከበራል - የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን - ኢዜአ አማርኛ
የመስቀል ደመራ በዓል ሃይማኖታዊ ሥነ-ስርዓቱን ጠብቆ ይከበራል - የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን
አዲስ አበባ መስከረም 16/2013 (ኢዜአ) የመሰቀል ደመራ በዓል ሃይማኖታዊ ሥነ-ስርዓት ሳይጓደል እንደሚከበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስታውቃለች።
በቤተክርስቲያኗ የፓትሪያርኩ ልዩ ፅህፈት ቤትና የውጭ ጉዳዮች የበላይ ኃላፊ ብጹዕ አቡነ አረጋዊ /ዶክተር/ የመስቀል ደመራ በዓል አከባበርን አስመልክተው ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በዓሉ ከ300 ዓመታት በላይ ጠፍቶ የቆየውና በንግሥት ዕሌኒ አማካኝነት የተገኘው መስቀል የሚዘከርበት ሲሆን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም ደመራ በመደመር በታላቅ መንፈሳዊ ሥነ-ስርዓት ይከበራል።
ብፁዕነታቸው የመስቀል በዓል መሰረቱ "ጌታችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው" ሲሉ ይጀምራሉ።
ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል ተዓምራዊነትና በክርስቲያኖች ዘንድ የተሰጠውን ከፍተኛ ክብር የተመለከቱ አይሁድ መስቀሉን በአንድ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ እንዲቀበር አደረጉ።
የአካባቢው ነዋሪዎች በየቀኑ ቆሻሻ ስለሚጥሉበትም ቦታው ወደ ተራራነት ተቀየረ፤ ምንም እንኳን መስቀሉን ለማውጣት ባይችሉም በኢየሩሳሌም የነበሩ ክርስቲያኖች ቦታውን ያውቁት ነበር።
በሰባ ዓመተ ምሕረት ኢየሩሳሌም በወረራ ስለጠፋች በዚያ የነበሩ ክርስቲያኖች ተሰደዱ፤ የተቀበረበትን ቦታ የሚያውቅ ባለመገኘቱም መስቀሉ ከ300 ዓመታት በላይ ተቀብሮ ኖረ።
በ326 ዓ.ም ቅዱስ መስቀሉን ለመፈለግ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ ያደረገችው የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ ጉብታ የሆነውን ሁሉ ብታስቆፍርም መስቀሉ ያለበትን ቦታ ማግኘት አልቻለችም።
የመስቀሉ መገኘት የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበርና አንድ ይሁድ አረጋዊ የታሪክ አዋቂ 'እንጨት ሰብስበሽ ዕጣን አፍስሺበት በእሳትም አያይዢው የዕጣኑ ጢስ ወደላይ ወጥቶ ወደታች ሲመለስ አቅጣጫውን አይተሽ አስቆፍሪው በዚህ ምልክት ታገኚዋለሽ" አላት እርሷም ይህንኑ አደረገች።
እንጨት ደምራና ዕጣን ጨምራ በእሳት ለኮሰችው፤ የዕጣኑ ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደ ታች ሲመለስ መስቀሉ ያለበትን ቦታ አመለከተ፤ ንግሥት ዕሌኒም ከመስከረም 17 ቀን አስጀምራ እስከ መጋቢት 10 ቀን ሌትና ቀን ለሰባት ወራት ያህል አስቆፈረች መስቀሉም ተገኘ።
በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦና ቤተክርስቲያን ተሠርቶ መስቀሉ መስከረም 17 ቀን 327 ዓ.ም ወደ ቤተክርስቲያኑ መግባቱን የገለጹት ብፁዕ አቡነ አረጋዊ "በቤተ ክርስቲያናችን ሁለቱም ዕለታት ይከበራሉ" ብለዋል።
የእምነቱ ተከታዮችም ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ለዓለም ቤዛና ድህነት የሆነበትን ዕለት በማሰብ በዓሉን በድምቀት ያከብሩታል።
ብጹዕ አቡነ አረጋዊ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የእየሱስ ክርስቶስ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱ 'ለኢትዮጵያ ክብር እየጨመረላትና ለአውደ በዓሉም ድምቀት እየሰጠው መጥቷል' ይላሉ።
ዛሬ የሚከበረውን የደመራ በዓል ሀይማኖታዊ ሂደት አስመልክተው ሲገልጹም 'ደመራ' የሚለው ቃል ደመረ ከሚለው የግዕዝ ቃል መምጣቱን ይህም ሰበሰበ፣ አከማቸ የሚል ትርጓሜ እንዳለውና ብዙ ወጣቶች በአንድ ላይ የሚሰበሰቡበት ማለት እንደሆነ ያስረዳሉ።
"የክርስትና እምነት ተከታዮች መስቀል የጥላቻ ኃይል መደምሰሻ፣ የጠብ ግርግዳ ማፍረሻ እንደሆነ
ያምናሉ" ያሉት አቡነ አረጋዊ መስቀልና ሠላም ተነጣጥለው እንደማይታዩ፤ መስቀል የተጣላ የሚታረቅበት፣ ሠላም የሚወርድበት፣ ይቅር ለእግዚአብሔር የሚባልበት ወቅት ነው ብለዋል።
ይህም "ጌታችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ተሰቅሎ ይቅርታ በማድረግ ሠላምና ምህረትን ለዓለም ካስተማረበት ምሳሌ ጋር የሚያያዝ ነው" ብለዋል።
የመስቀል በዓል የሕዝቦች አንድነት የሚጠናከርበት፣ የተራራቀ የሚገናኝበት መሆኑንም አክለዋል።
የዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓል በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በርካታ ሕዝብ በዋነኛው የበዓሉ ማክበሪያ መስቀል አደባባይ የማይሳተፍ ቢሆንም ሀይማኖታዊ ሥነ-ስርዓቱ ሳይጓደል እንደሚከበር ብፁዕ አቡነ አረጋዊ ገልጸዋል።
ብጹዕነታቸው ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የደመራና የመስቀል በዓል የሠላም፣ የደስታ፣ የበረከትና የመተሳሰብ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።