ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት ሰራተኞች ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የ1 ሚሊዮን ብር ቦንድ ገዙ

አዲስ አበባ መስከረም 15/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብአቶች ልማት ድርጅት ሰራተኞችና አመራሮች ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የ1 ሚሊዮን ብር የቦንድ ግዥ ፈፀሙ።

ድርጅቱ የገዛውን ቦንድ ለአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ያስረከበ ሲሆን በርክክብ ስነ-ስርአቱ ላይ የህዳሴ ግድብ ገቢ ማሰባሰቢያ ዋንጫን ለድርጅቱ አስረክቧል።

የድርጅቱ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ንጉሴ ገብረማሪያም በርክክብ ስነ-ስረአቱ ላይ ባደረጉት ንግግር  በርካታ ስራዎች የኃይል አቅርቦት ዝቅተኛ መሆን ስራው በተቀላጠፈ መልኩ እንዳይከናወን መሰናከል እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።

በመሆኑም የህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን መሆን ለድርጅቱም ሆነ በኢንዱሰትሪው ዘርፍ ለተሰማሩ ሌሎች ተቋማት አይነተኛ ጥቅም አለው ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ እንዲጠናቀቅ ድርጅቱ የሚያደርገውን ድጋፍ ያጠናክራል ያሉት አቶ ንጉሴ በሰራተኞቹና በሃላፊዎች ትብብር የ1 ሚሊዮን ብር ቦንድ ግዥ መፈፀሙን ተናግረዋል።

የአራዳ ክፈለ ከተማ ወረዳ 2 ብልጽግና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚደቅሳ  ከበደ በበኩላቸው የድርጅቱ ሰራተኞች ለግድቡ ግንባታ እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ አድንቀዋል።

የገቢ ማሰባሰቢያ ዋንጫው በተዘዋረባቸው ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች የሚስተዋለው የማህበረሰብ ቁርጠኝነትም የህዳሴ ግድብ የባለቤትነት ስሜትን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በሃምሌና ነሃሴ 2012 ዓ.ም በወረዳው በተደረገው የሃብት ማሰባሰብ ስራ 260 ሚሊዮን ብር በቦንድና በስጦታ መሰብሰቡንም አስታውሰዋል።

በአጠቃላይ እስካሁን በክፍለ ከተማው ዋንጫው በቆየበት ግዜ ከ4 ንጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም