ለኢትዮጵያ ቱሪዝም እድገት በገጠር ቱሪዝም ልማት ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ ቱሪዝም እድገት በገጠር ቱሪዝም ልማት ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ተባለ
አዲስ አበባ መስከረም 15/2020(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቱሪዝም በሚገባው ልክ እንዲያድግና ሀገሪቱም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ በገጠር ቱሪዝም ልማት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በቱሪዝም ዘርፍ ጉዳዮች ዙሪያ በሱባ መናገሻ ደን ከተለያዩ የዘርፉ አካላት ጋር የውይይት አካሂዷል።
ኢትዮጵያ ያልተነኩ እና ብዙ መስራት የሚቻልባቸው የቱሪዝም ሃብት ያላት ብትሆንም በሚገባው ልክ ግን አልተጠቀመችበትም።
ዘርፉ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ከሚደግፉና ከፍትኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከሚያስገኙ ሴክተሮች መካከል አንደኛው ነው።
ይሁንና አገሪቱ ካሏት ቅርሶችና ሃብቶች አኳያ ዘርፉን በሚፈለገው ደረጃ ማሳደግና ከዘርፉ የሚገኘውንም ጥቅም ማጎልበት አለመቻሉን ይገልጻሉ።
አብዛኛው ኢንቨስትመንት ትኩረቱን ያደረገው በከተሞችና በተለመዱ አካባቢዎች ላይ ሲሆን የገጠሩ ቱሪዝም ማልማት ላይ ግን በሚገባው ልክ እንዳልተሰራበትም የዘርፉ አካላት ይገለፃል።
በዚህም በገጠራማው የሀገሪቱ ክፍሎች በርካታ ሊሰራባቸው የሚገቡ የቱሪስት መዳረሻዎች ያሉ በመሆናቸው የገጠር ቱሪዝም ልማትን ማስፋፋትና ማጠናከር ይገባልም ብለዋል።
ባለሃብቶችና ሌሎችም የዘርፉ ማህበረሰብ አባላት ከከተሞች ባሻገር በገጠሩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ መዳረሻዎች ላይ ኢንቨስት ማድረግ እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
ይህም የአካባቢውን ማህበረሰብ ክፍሎች በመሰረተ ልማት፣ በስራ እድል ፈጠራና በሌሎችም ተጠቃሚ እንዲሆን በማገዝ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ያብራራሉ።
በመሆኑም የገጠር ቱሪዝምን በማስፋፋትና በማልማት የዘርፉን እድገትና የህዝቦችንም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማጎልበት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የአለም የቱሪዝም ቀን ዘንድሮ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ41ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ33ኛ "ቱሪዝም እና ገጠር ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ ይከበራል።