በአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አጠቃቀም ላይ ሰፊ ክፍተት መኖሩን አንድ ጥናት አመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
በአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አጠቃቀም ላይ ሰፊ ክፍተት መኖሩን አንድ ጥናት አመለከተ
አዲስ አበባ መስከረም 15/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አጠቃቀም ላይ ሰፊ ክፍተት መኖሩን ኢዜአ ያደረገው ጥናት አመለከተ።
የኮሮናቫይረስን በመከላከል ሂደት ማህበረሰቡ እየተዘናጋ መሆኑንም ጥናቱ ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዙሪያ የህብረተሰቡን የግንዛቤ ደረጃና አተያይ ለመገንዘብ አንድ የዳሰሳ ጥናት አድርጓል።
ጥናቱን በአዲስ አበባ፣ በጋምቤላ፣ ሓረሪ፣ ኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመጠየቅ የተሰራ ነው።
የጥናቱ ዓላማም ኮቪድ-19 ለመከላከል ዋና ዋና መርሆች ናቸው በተባሉት የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል አጠቃቀም፣ አካላዊ ርቀትን መጠበቅና የእጅ ንጽህና በአግባቡ መጠበቅ ላይ ትኩረት ያደረገ እንደሆነ ተብራርቷል።
በጥናቱ መሰረት የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብልን ህብረተሰቡ በብዛት እየተጠቀመና ባህል እያደረገው መሆኑ ተመልክቷል።
ይሁን እንጂ የጭምብል አጠቃቀም ክፍተቶች በስፋት መኖራቸው ተረጋግጧል።
የሚታጠቡትንም የማይታጠቡትንም ጭምብሎች በንጽህና ያለመጠቀም፣ ከአገልግሎት ጊዜው በላይ መጠቀምና አወጋገድ ላይ ሰፊ ክፍተቶች መኖራቸው በጥናቱ ተረጋግጧል።
በእነዚህና መሰል ችግሮች ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮችንና መዘናጋቶችን ለመቅረፍ ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎችን ማከናወን እነደሚያስፈልግ ተመላክቷል።
ሌላው አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ ወረርሽኙን መከላከል እንደሚቻል ህብረተሰቡ የተረዳ ቢሆንም በአግባቡ ለመተግበር አዳጋች መሆኑም ተገልጿል።
በተለይም በትራንስፖርት አገልግሎት፣ በገበያ ስፍራና በሌሎች አካባቢዎች አካላዊ ርቀትን ጠብቆ መንቀሳቀስ አስቸጋሪ መሆኑ ተመልክቷል።
የእጅ ንጽህናን በመጠበቅ በኩል ደግሞ ጥናቱ በተካሄደባቸው በሁሉም አካባቢዎች ወረርሽኙ በነበረበት ወቅት የነበረው የእጅ ንጽህና የመጠበቅ ተግባር መቀዛቀዙን ያሳያል።
ይህም የህብረተሰቡን መዘናጋትና ለጉዳዩ ክብደት አለመስጠትን የሚያመለክት መሆኑ ታውቋል።
የእጅ ንጽህናን በአግባቡ ባለመጠበቅ የወረርሽኙ መስፋፋትና ስርጭት አሁንም በስፋት ሊዛመት ይችላል የሚል ትንበያ በጥናቱ ላይ ተመልክቷል።
በመሆኑም በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች የግንዛቤ የማስጨበጥ፣ የክትትልና የቁጥጥር ስራው መጠናከር እንዳለበት ተጠቁሟል።
በተለይም ትምህርት ለማስጀመር መንግስት እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ተከትሎ ከፍተኛ ጥንቃቄና አማራጮችን ማስፋት ያስፈልጋል ተብሏል።
ህዝብ የሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ላይ በልዩ ሁኔታ ማስፋፊያ የሚደረግባቸውን በመለየት ማሻሻያ ማድረግና ቁጥጥር የሚደረግባቸው አካላት ላይም እንዲሁ ቀደም ሲል እየተከናወነ የነበረው ስራ ሊጠናከር እንደሚገባ ጥናቱ ጠቁሟል።