ቀጥታ፡

ህብረተሰቡ የደመራ በዓልን ሲያከብር ለእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መንስኤ ከሚሆኑ ነገሮች እንዲጠነቀቅ ተጠየቀ

አዲስ አበባ መስከረም 15/2013 (ኢዜአ) የደመራ በዓል ሲከበር ማህበረሰቡ ለእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መንስኤ ከሚሆኑ ነገሮች ጥንቃቄ እንዲደረግ የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ።

የመስቀል ዋዜማ የደመራ በዓል እና የመስቀል በዓል ነገና ከነገ በስቲያ ይከበራል።

የአዲስ አበባ የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት የቡድን መሪ አቶ ጉልላት ጌታነህ  የደመራ በዓል ሊከሰት የሚችል አደጋን ለመከላከል የሚያስችለውን የቅድመ ዝግጅት ስራ ማጠናቀቁን ለኢዜአ ገልጸዋል።

አደጋ ቢከሰት ለመቆጣጠር በቂ ባለሙያዎች ዝግጁ ሲሆኑ እሳት ለማጥፋት የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችና ቁሳቁሶችም ተሟልተዋል ብለዋል።

የህክምና እርዳታ የሚሰጡ ነርሶችና አምቡላንሶችም ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ውሃ ፍሳሽ ባለስልጣን አደጋ ቢከሰት የውሃ አቅርቦትን ተደራሽ ማድረግ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የኤሌክትሪክ መስመር ላይ ቃጠሎ ቢደርስ ሃይል በሚያቋርጥበት ሁኔታ ላይ የጋራ ዝግጅት መደረጉንም አመልክተዋል።

ከሁለቱ ተቋማት ጋር የሚሰሩ ስራዎች የእሳት አደጋ ቢከሰት በፍጥነት ለመቆጣጠር እንደሚያስችል ነው አቶ ጉልላት ያስረዱት።

ቃጠሎ እንዳይፈጠር ቀድሞ ጥንቃቄ ለማድረግ ደመራ የሚለኮስበት ቦታ ከኤሌክትሪክ መስመሮች እርቆ ሊሆን እንደሚገባውም አሳስበዋል።

ደመራው በሚበራበት ሰአት ሌሎች ተቀጣጣይ ነገሮችን ባለመጠቀም የእሳት አደጋ እንዳይከሰት ህብረተሰቡ ሊጠነቀቅ ይገባልም ብለዋል።

ከዚህ በፊት የደመራ በዓል በሚከበርበት ወቅት በሚከሰቱ የእሳት አደጋዎች የቤትና የንብረት ቃጠሎዎች አጋጥመው እንደነበር አስታውሰዋል።

በዘንድሮው የደመራ በዓል መሰል አደጋዎች እንዳይከሰቱ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በደመራ አከባበር ላይ የእሳት አደጋ ቢያጋጥም በነጻ የስልክ መስመር 939፤

በቀጥታ የስልክ መስመሮች 011 155 53 00 ወይም በ 011 156 86 01 ደውሎ ማሳወቅ እንደሚችልም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም