የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ የሞጣ ቤት እምነቶችን መልሶ ለመገንባት ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ የሞጣ ቤት እምነቶችን መልሶ ለመገንባት ድጋፍ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቀረበ
አዲስ አበባ መስከረም 14/2013 የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር-ቤት በሞጣ ከተማ ጥቃት ደርሶባቸው የነበሩ ቤተ እምነቶችን መልሶ ለመገንባት በተደረገው የሃብት ማሰባሰብ ድጋፍ ላደረጉ አካላት ሁሉ ምስጋና አቀረበ፡፡
ምክር ቤቱም በሞጣ ከተማ ጥቃት የደረሰባቸውን ቤተ እምነቶችና የሙስሊም ማህበረሰቦችን ለመደገፍ ሲያከናውናቸው የነበሩ ስራዎችን በሚመለከት ዛሬ በጽህፈት ቤቱ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር-ቤት ዋና ጸሃፊ እና የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ ሸህ ቃሲም መሐመድ ታጁዲን በመግለጫቸው በድጋፉ ለተሳተፉ ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
"በቤተ እምነቶችና የአካባቢው እስልምና እምነት ተከታዮች ላይ በወቅቱ ደርሶ የነበረውን ጥቃት ተከትሎ ጥር 22 ቀን 2012 ዓ.ም በተጠራው የሃብት ማሰባሰብ መርሃ ግብር የተሳተፉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊን አሻራቸው በደማቅ ታሪክ ተጽፎ ሲዘከር ይኖራል" ብለዋል፡፡
በገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ በተጀመረበት እለት አርብ ጥር 22 ቀን 2012 ዓ.ም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሃይማኖት፣ ብሔር እና የፖለቲካ አመለካከት ሳይገድባቸው ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ምክር ቤቱ የህዝቡን ፍላጎት በመረዳት እለቷ "ጥር 22 ፋውንዴሽን" ተሰኝታ እውቅና አግኝቶ እንዲቋቋም መወሰኑንም ጠቁመዋል፡፡
ፍውንዴሽኑም በቀጣይ በመላ አለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር በአራቱም የአገሪቱ ማእዘናት የሚያጋጥሙ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታትና የሞራል ስብራቶችን ለመጠገን የሚሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ በአገር ውስጥ ድጋፉ 265 ሚሊዮን 460 ሺህ 942 ብር እንዲሁም ከውጭ 454 ሺህ 316 የአሜሪካን ዶላር መሰብሰቡን አስረድተዋል፡፡
በጥቃቱ ሰለባ ለሆኑ ቤተ እምነቶችና ተጎጂ አካላት የሞራልና የንብረት ጉዳት ለመጠገን ሲሰራ መቆየቱንና እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
ይህ መግለጫ እስከተሰጠበት ጊዜ ድረስ ከተሰበሰበው ገንዘብ ተጎጂዎችን ለማቋቋምና ተያያዥ ጉዳዮችን ለማከናወን ከ72 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ሆኗል ብለዋል።
በውጭ አገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተላኩ ቁርኣን፣ አልባሳት፣ ኪታቦችንና ለሞጣ መስጊዶች ድጋፍ መደረጉንም በመግለጫቸው አመላክተዋል፡፡
በሂደቱ የሞጣ ተወላጆችን ያካተተ የሰላም ልዑክ ወደ ስፍራው በማቅናት ከከተማ አስተዳደሩ ስራ ኃላፊዎችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ የትኛውንም ዓይነት መረጃ የሚፈልግ አካል ቢኖር የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር-ቤቱን መጠየቅ እንደሚቻል በመግለጫው ተመላክቷል፡፡