የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ትምህርት ዳግም በሚጀመርበት ሁኔታ ላይ ምክክር እየተካሄደ ነው

289

አዲስ አበባ መስከረም 14/2013 (ኢዜአ) በኮቪድ-19 ምክንያት ተቋርጦ የቆየው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ትምህርት ዳግም በሚጀመርበት ሁኔታ ላይ ምክክር እየተካሄደ ነው።

በውይይቱ ላይ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የኢፌዴሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ አስቸኳይ ስብሰባውን በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለወራት የተቋረጠውን ትምህርት ዝግጅት ተደርጎ በ2013 ዓ.ም እንዲጀመር ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።

በዚህም መሰረት ትምህርቱን ማስጀመር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ውይይታቸውን በአዲስ አበባ እያካሄዱ ይገኛሉ።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በውይይቱ መክፈቻ ላይ እንዳሉት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር በወቅቱ የትምህርት ተቋማትን በመዝጋት የወሰደችው እርምጃ ውጤታማ ነበር።

አሁን ላይ ግን የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጣቸው መስፈርቶች መሰረት በጥንቃቄ በመከላከል ወደ መደበኛ ስራ መመለስ ይገባል ብለዋል።

በቫይረሱ ምክንያት የተቋረጠውን የመማር ማስተማር ሂደት ለማስቀጠል የሁላችንንም ጥረትና ሃላፊነት ይጠይቃል ነው ያሉት።

በመሆኑም የወረርሽኙን ስርጭት በመከላከል መደበኛ ተግባራችንን እየተወጣን በተለይ ትምህርት እንዲጀመር ማድረግ አለብን ብለዋል።

የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ፤ የተቋረጠው ትምህርት ዳግም እንዲጀመር ዝግጅት መጀመሩን አረጋግጠዋል።

ወረርሽኙን ባስከተለው ችግር 80 የቴክኒክ ተቋማትና 40 የአይሲቲ ተቋማት መሠረተ ልማታቸውን ለማሟላት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እያንዳንዱ ኮሌጅ ያለውን አቅምና ዝግጅት በመለየት የመውጫና የመግቢያ ሰዓታቸውን በማጣጣም እንዲሠሩ አቅጣጫ ተቀምጧል።

እንደ ኮሌጆቹ ነባራዊ ሁኔታ ሠልጣኞችና አሠልጣኞች ከተለመደው አሰራር የተለየ መመሪያ እንዲያዘጋጁም ተጠይቀዋል።

የውይይት መድረኩ ዛሬና ነገ የሚካሄድ ሲሆን በመጨረሻም በአዲስ አበባ ለኮሮና ወረርሽኝ ምላሽ በመስጠት ዝግጅት ያደረጉ የተመረጡ ኮሌጆች ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም