በመስቀል አደባባይ የደመራ በዓል የሚከበርበት ስፍራ ፅዳት ተከናወነ - ኢዜአ አማርኛ
በመስቀል አደባባይ የደመራ በዓል የሚከበርበት ስፍራ ፅዳት ተከናወነ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 14/2013 ( ኢዜአ) በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የደመራ በዓል የሚከበርበት ስፍራ በሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስተባባሪነት የጽዳት ስራ ተከናወነ።
የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክት ግንባታ አሁን ላይ 70 በመቶ የደረሰ ሲሆን የደመራ በዓል ማክበሪያ ቦታው ዝግጁ እንዲሆን ተደርጓል።
የበዓሉ ማክበሪያ ስፍራም በሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አስተባባሪነት በዛሬው እለት እንዲፀዳ ተደርጓል።
ፅዳቱን የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ የተለያዩ እምነት ተከታይ ወጣቶች የጽዳት ሰራተኞችና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አከናውነዋል።
በፅዳቱ ላይ የተሳተፉት የአዲስ ከተማ ከፍለ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ መጋቢ ሃይማኖት ቀሲስ ዓለሙ ሲራክ እንዳሉት የደመራ በዓል የዓለም ቅርስ በመሆኑ ለበዓሉ አከባበር በጋራ ማፅዳታችን ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል።
ወቅቱ የኮሮናቫይረስ ስርጭት እየሰፋ የመጣበት በመሆኑ በስፍራው በርካታ ሰዎች መሰባሰብ ስለማይችሉ በዓሉን በቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት በየቤታቸው ሆነው መከታተል ይኖርብናል ብለዋል።
ወደ መስቀል አደባባይ የሚመጡ የበዓሉ ተሳታፊዎችም እራሳቸውን ከኮሮናቫይረስ በመጠበቅና ርቀታቸውን በመጠበቅና ሊሆን ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ካውንስል ጠቅላይ ጸሐፊ ቄስ ደረጀ ጀንበሩ በፅዳቱ ላይ በመሳተፋቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በዚህች ሀገር ላይ ለዘመናት ክርትስትናን ያስተማረች ናት ያሉት ጠቅላይ ጸሃፊው መስቀልንም በብዙ መልኩ ስታስተምር ማቆየቷን ተናግረዋል።
በፅዳቱ ላይ የተሳተፉትም ይህን ስታደረግ ለኖረች ቤተክርስቲያንና ያላቸውን አክብሮትና አብሮነት ለመግለጽ እንደሆነ ነው የገለጹት።
መሰቀል ከኢትዮጵያም አልፎ የዓለም ቅርስ በመሆኑ ለጋራ ሃብታቸን በጋራ ልንቆም ይገባልም ብለዋል።
በጽዳት መርሃ ገበሩ ላይ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችን ጨምሮ የክርስትና አማኞች፣ አባቶች፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ሌሎችም ተሳትፈዋል።
በእለቱ ከጽዳቱ በተጨማሪ በስፍራው የፀረ-ተህዋስ ኬሚካል ርጭት ተከናውኗል።
የፊታችን ቅዳሜ መስከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም የደመራ በዓል የሚከበርበት እለት ሲሆን በአዲስ አበባም በመስቀል አደባባይ ይከበራል።