ቀጥታ፡

በመዲናዋ የመስቀል በዓል ሲከበር አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ ፖሊስ ይፋ አደረገ

አዲስ አበባ መስከረም 14/2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ለሚከበረው የመስቀል በዓል የይለፍ ባጅ ካላቸው ተሽከርካሪዎች በስተቀር ወደ ለሌሎች ዝግ የሚደረግ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ።

የደመራ በዓል ተጀምሮ አስከሚጠናቀቅ ለአሽከርካሪዎች ዝግ የተደረጉ መንገዶችንም ፖሊስ ይፋ አድርጓል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የ2013 ዓ.ም የመስቀል በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን የፀጥታ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን አስታውቋል።

የፊታችን ቅዳሜ መስከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ የሚከበረው የደመራ በዓል ተጀምሮ አስከሚጠናቀቅ የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙም ፖሊስ ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡

በዚህም መሰረት ከቦሌ አየር መንገድ በሚሊኒየም አዳራሽ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ደንበል ሲቲ ሴንተር ኦሎምፒያ አደባባይ አካባቢ ይለፍ ለሌላቸው ተሽከርካሪዎች ከቀኑ 5 ሰዓት ጀምሮ ዝግጅቱ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ዝግ ይደረጋል ተብሏል።

ከመገናኛ ፣ በሃያ ሁለት ወደ መስቀል አደባባይ እንዲሁም ከቦሌ መድሃኒያለም፣ በአትላስ ሆቴል ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ኡራኤል ቤተ-ክርስቲያ አካባቢ እንዲሁም ከአራት ኪሎ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድም እንዲሁ።

ከቸርችል ጎዳና ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ አገር አስተዳደር መብራት ወይም ኢሚግሬሽን መ/ቤት አካባቢና ከተክለ ሃይማኖት በሜትዎሮሎጂ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድም ዝግ ይሆናል።

ከተክለ ሀይማኖት፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል፣ ከጌጃ ሰፈር፣ ጤና ሚኒስቴር፣ ብሄራዊ ቴአትር፣ ጎማ ቁጠባ፣ ከሳሪስ በጎተራ የቀድሞ አራተኛ ክፍለ ጦር አካባቢ፣ ከጦር ኃይሎች፣ ልደታ፣ ፖሊስ ሆስፒታል ፣ ሜክሲኮ ፣ ለገሀር መብራት የሚወስደው መንገድ ለገሃር መብራት አካባቢ ይለፍ ለሌላቸው ተሽከርካሪዎች ከቀኑ 5 ሰዓት ጀምሮ ዝግጅቱ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ዝግ እንደሚሆን ፖሊስ ኮሚሽኑ አስታውቋል።

እንደ ፖሊስ መግለጫ ደመራው የሚደመርበት መስቀል አደባባይ እና ከቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ወደ ስታዲዬም እንዲሁም ከሃራምቤ ሆቴል ወደ ሴንጅ ዮሴፍ የሚያቋርጠው መስቀለኛ መንገድ ለበዓሉ በሚደረገው ዝግጅት ምክንያት ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ ዝግ የሚደረግ ይሆናል፡፡

በመሆኑም ህብረተሰቡ ከፖሊስ የተሰጠውን መረጃ ተገንዝቦ የትራፊክ ፖሊስ አባላት በሚጠቁሙት አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀም እና ለትራፊክ ፖሊስ አባላት ትዕዛዝ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ፖሊስ ኮሚሽኑ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም