የጅቡቲ መንግስት በአፋር ጎርፍ ጉዳት ላደረሰባቸው ወገኖች ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ

96

ሠመራ፣ መስከረም 13/2013 (ኢዜአ) የጂቡቲ መንግስት በአፋር ክልል ጎርፍ ጉዳት ላደረሰባቸው ወገኖች የሚውል ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ምግብና መድኃኒት ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉን ለአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ያስረከቡት የጂቡቲ መንግስት ልኡካን ቡድን መሪ አቶ ሀሰን ሁመድ ናቸው።

አቶ ሀሰን በዚህ ወቅት በክልሉ በተከሰተው ጎርፍ  የደረሰው ጉዳት ከባድ መሆኑን ከአመራሮቹ ጋር ባደረጉት ውይይት መረዳታቸውን  ተናግረዋል።

የፌዴራልና የክልሉ መንግስት ለተጎጂዎቹ ከእለት ደራሽ እርዳታ ጀምሮ በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያደርገውን  ጥረት የጀብቲ መንግስትም  የሚችለውን አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።

ለጊዜው መንግስታቸው ምግብ፣ መድኃኒት አልባሳት ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶች ለአፋር ክልል ማበርከቱን ገልጸው፤ በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ  እንደሚቀጥል አስታወቀዋል።

የአፋር ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው የአፋርና ጂቡቲ ህዝቦች በደምና በባህል የተሳሰሰሩ ዘመናት የተሻገረ ጠንካራ ቤተሰባዊ መስተጋብር ያላቸው ወንድማማች  ህዝቦች ናቸው ብለዋል።

በክልሉ ድጋፍ ሲያደርጉ ዛሬ የመጀመሪያቸው ሳይሆን ወትሮም የነበረ መልካም እሴት መሆኑን ተናግረዋል።

የተደረገው ድጋፍ በክልሉ ጎርፍ ጉዳት ያደረሰባቸው ወገኖችን ችግር ለማቃለል እንደሚያግዝና ለድጋፉም በተጎጂዎቹ ስም ለጂቡቲ ልኡካንና ለሀገሪቱ መንግስት ምስጋና አቅርበዋል።

በአፋር ክልል ጎርፍ ጉዳት ካደረሰባቸው ከ240 ሺህ በላይ ሰዎች መካከል 144 ሺህ ያህሉ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ መሆናቸውን ከክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም