ቀጥታ፡

በተያዘው የበጀት ዓመት ለ3 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለማመቻቸት እየተሰራ ነው

ድሬዳዋ መስከረም 13/2013 (ኢዜአ) በሀገሪቱ በተያዘው የበጀት ዓመት 3 ሚሊዮን ለሚሆኑ የሥራ አጥ ዜጎች የሥራ ዕድል ለማመቻቸት እየተሰራ መሆኑን የፌደራል የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽነር አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገለጹ።

ኮሚሽነሩ ከድሬዳዋ አስተዳደር አመራሮች በበጀት ዓመቱ ዕቅድ ዙሪያ ትናንት በተወያዩበት ወቅት እንዳሉት የሚፈለገው ሰላምና ዕድገት ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ፍሬያማ እንዲሆን በአሳሳቢ ደረጃ እየጨመረ ለሚገኘው የስራ አጦችን ቁጥር ለመቀነስ መፍትሄ ያስፈልገዋል፡፡

ችግሩን ለማቃለል ያለውን ምቹ የተፈጥሮ ሃብት፣ እውቀትና የሰው ኃይል በመጠቀም ተግቶ መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

በአዲሱ ትውልድ ውስጥ የሥራ ክቡርነትን በማስረጽና ለስራ አጡ የሥራ ዕድል በመፍጠር በሀገሩ ላይ ተስፋ የሚጥል ወጣት መገንባት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ 

ኮሚሽኑ በበጀት ዓመቱ በተለያዩ መስኮች 3 ሚሊዮን የሚሆኑ የሀገሪቱ ዜጎች የሥራ ዕድል ለማመቻቸት አቅዶ እየሰራ መሆኑን አቶ ንጉሱ ገልጸዋል፡፡

ለእቅዱ መሳካት አመራሩ አዳዲስ አሰራሮችንና አደረጃጀቶችን በመዘርጋት፤ በተቀናጀና በተናበበ መንገድ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ መረባረብ እንዳለበት አመልክተዋል።

ከድሬዳዋ አመራሮች ጋር በተወያየበት ወቅት በበጀት ዓመቱ በድሬዳዋ ለ24 ሺህ ሰዎች የሥራ ዕድል ለማመቻቸት እንደታቀደ መረዳታቸውን ጠቅሰው ውጥኑ እንዲሳካ ድጋፍ እንደሚደረግ ኮሚሽኑ አስታውቀዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተያዘው ዕቅድ መሳካት ከሁሉም ክልሎች አመራሮች ጋር ውይይት ይደረጋል ብለዋል፡፡ 

በኮሚሽኑ የሥራ ዕድል ፈጠራ ክትትልና አቅም ግንባታ ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ታደሰ ባለፈው ዓመት በግብርና ፣ ኢንዱስትሪ፣ ማኑፋክቸሪንግና ሌሎች መስኮች ከሶስት ሚሊዮን 400 ሺህ በላይ ሰዎች የሥራ ዕድል ማመቻቸት መቻሉን አውስተዋል፡፡

ከነዚህ ውስጥ 62 በመቶው በቋሚነት የሥራ ዕድል ያገኙ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

እንደ ሀገር ብሎም እንደ ድሬዳዋ የተወጠነውን ለማሳካት ነባር ኢንተርፕራይዞች በኮሮና ሣቢያ ከገበያና ማምረት ስራ እንዳይወጡ መደገፍ፣ ለአዳዲስ ኢንተርፕራይዞች የብድር ፣ የሥልጠና ፣ የመሸጫና የማምረቻ፣ ድጋፎችን መስጠት ይገባል፤ አመራሩ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ማጠናከር ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ በበኩላቸው ድሬዳዋ በሀገር ደረጃ በሥራ አጥ ቁጥር ቀዳሚ የሆነችው ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመምጣት ወደ ውጪ ለመውጣት አስበው ያልተሳካላቸው ወጣቶች በከተማዋ በመብዛታቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ይህንን በመረዳት በበጀት ዓመቱ 24ሺ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል ለማመቻቸት አስተዳደሩ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ድጋፍ የፌዴራል መንግስት  እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል፡፡

ወደ ውጭ  የሚደረጉ የሥራ ስምሪቶች ፍሬያማና ለሀገር የሚጠቅሙ እንዲሆኑ ወጣቶችን በተገቢው መንገድ የእውቀትና የተለያዩ ቋንቋዎች ባለቤት የማድረግ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡

በድሬዳዋ የሚገኙ ኢንተርፕራይዞችና ማህበራት ውጤታማ ተግባራት እንዲያከናውኑ ባለፉት ዓመታት ተገንብተው የተጠናቀቁ የማምረቻና የመሸጫ ቦታዎች እንደሚሰጣቸው የገለጹት ደግሞ የአስተዳደሩ የከተማ ሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ማርቆስ ባዩህ ናቸው፡፡

"የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዘንድሮ በተሻለ መንገድ ይጠናከራል "ብለዋል፡፡

በኮሚሽነር ንጉሱ ጥላሁን የተመራው ልሁካን በድሬዳዋ ከተማ በሥራ ዕድል ፈጠራ የተከናወኑ ተግባራትን ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም