ቀጥታ፡

ህብረተሰቡ ፈጥኖ ወደ ባንክ በመምጣት ነባሩን የብር ኖት እንዲቀይር ተጠየቀ

መቀሌ፣ መስከረም 13/2013 (ኢዜአ ) ህብረተሰቡ ፈጥኖ ወደ ባንኮች በመምጣት ነባሩን የብር ኖት በአዲሱ እንዲቀይር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመቀሌ ቅርንጫፍ ጠየቀ።

በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመቐለ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ሰዋሰው ለኢዜአ እንደገለጹት ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የተላኩ ባለ 200፣ ባለ 100፣ ባለ 50 እና  ባለ 10 ብር አዲስ የብር ኖቶች ከትላንት ጀምሮ ወደ ክልሉ ደርሰዋል ።

"ነባሮቹን የብር ኖቶች በአዲሱ ለመቀየር በፋይናንስ ተቋማት በኩል በቂ ዝግጅት ተደርጓል" ያሉት ስራ አስኪያጁ አዲሶቹ የብር ኖቶች ለሁሉም የመንግስትና የግል ባንኮች እንዲሁም ለማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት እየተሰራጩ መሆኑን ተናግረዋል ።

ህብረተሰቡ በቂ ጊዜ አለኝ በሚል ሳይዘናጋ በቤቱ ያስቀመጠውን ነባር የብር ኖት ወደ ባንኮች በመምጣት እንዲቀይር ጠይቀዋል ።

የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎችም በቤታቸው የተቀመጡ ነባር የብር ኖቶችን ወደ ባንክ በመሄድ እየለወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል ።

የከተማው ነዋሪ ወጣት ሮቤል ስዩም  እንደገለጸው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዓዲሓቂ ቅርንጫፍ በመሄድ  በቤቱ አስቀምጦት የነበረውን 20 ሺህ አሮጌ የብር ኖት በአዲሱ መቀየሩን ተናግሯል ።

የቀየረውን አዲስ የብር ኖት በባንክ ሒሳብ ደብተሩ ማስቀመጡን ገልጿል ።

በቤታቸው ያስቀመጡትን የብር ኖት በአዲሱ ለመቀየር በባንክ ወረፋ ይዘው በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ  በመቀሌ የዓዲ-ሐ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሃገረይ ባወቀ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም