ተደጋጋሚ የጸጥታ ችግር የሚታይበት የመተከል ዞን የአመራር መዋቅር እንደገና ይደራጃል

አሶሳ መስከረም 12/2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የተከሰተውን የጸጥታ ችግር በመመከት ህብረተሰቡን በተሻለ የሚያገለግል አዲስ የአመራር መዋቅር እንደገና የሚደራጅበት እና በችግሩ የተሳተፉትን ተጠያቂ የሚያደርግ ግምገማ በነገው ዕለት እንደሚጀመር ተገለጸ፡፡

የክልሉ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ መለሰ በየነ ዛሬ ለኢዜአ እንዳስታወቁት በዞኑ ቡለን እና ወምበራ ወረዳዎች በተከሰተው ግጭት ምክንያት በተለይም የወረዳ አመራሩ ሃላፊነቱን በሚገባ አልተወጣም።

“ችግሩን ለማጥራት ነገ የሚጀመር እና እስከ ሁለት ቀናት ሊፈጅ የሚችል የግምገማ መድረክ በዞኑ ከተማ ግልገልበለስ ይካሄዳል” ብለዋል። 

ግምገማው የጸጥታ ችግር የተከሰተባቸውን ቡለን፣ ወምበራ፣ ጉባ እና ሌሎችም የዞኑ ወረዳዎች አመራሮችን ጭምር እንደሚያካትት አስረድተዋል፡፡

በግምገማው በዞኑ የጸጥታ ችግሮችን በዘላቂነት በመመከት ህብረተሰቡን በተሻለ መንገድ መምራት የሚያስችል የአመራር መዋቅር እንደገና የማደራጀት ስራ እንደሚከናወን ጠቅሰዋል።

“በዞኑ ግጭት በተከሰተበት ወቅት ሁሉም አመራሮች በችግሩ ላይ ተመሳሳይ አቋም ይዘው እየታገሉ አልነበሩም” ያሉት አቶ መለሰ አንዳንዶቹም የጸረ-ሰላም ኃይሎችን አቋም የያዙ እንደሆኑ አመልክተዋል።

“በዚህ ደረጃ የሚገኝን የአመራር መዋቅር ይዞ መቀጠል ችግሩን እንዲባባስ መፍቀድ ነው” ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በግምገማው ኃላፊነታቸውን ያልተወጡትን በመለየት ከሃላፊነት ማንሳት ብቻ ሳይሆን ማስረጃ በማሰባሰብ በህግ እስከ መጠየቅ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም