አገር በቀል የጸረ-እምቦጭ መድኃኒት ግኝቱ ወቅቱ የሚጠይቀው መፍትሄ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አገር በቀል የጸረ-እምቦጭ መድኃኒት ግኝቱ ወቅቱ የሚጠይቀው መፍትሄ ነው
አዲስ አበባ መስከረም 12/2013 (ኢዜአ) አገር በቀል የጸረ እምቦጭ መድኃኒት ግኝት እምቦጭን ለማጥፋት አገራዊ የምርምር ውጤትን ይዞ መቅረብ ወቅቱ የሚጠይቀው መፍትሄ መሆኑን ያሳያል ሲል የባህል ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።
አገር በቀል የጸረ-እምቦጭ መድኃኒት ግኝቱን በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ጥቅም ላይ ለማዋል በትኩረት እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ሊቃውንትና ምሁራን ማህበር አገር በቀል የፀረ-እምቦጭ መድኃኒት ምርምር የደረሰበትን ደረጃና ቀጣይ ሥራዎቹ ላይ ማብራሪያ ሰጥቷል።
በማብራሪያው ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯን ወክለው ንግግር ያደረጉት በሚኒስቴሩ የፕሮጀክቶች አማካሪ ዶክተር ታደለ ፋንታሁን የተበታተኑ አገር በቀል እውቀቶችን በማሰባሰብ አገሪቱን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለእዚህም የምርምር ሥራው ፖሊሲ ወጥቶለት መስራት የሚያስችል ማዕቀፍ በሚኒስቴሩ በኩል መዘጋጀቱን ነው የጠቆሙት።
በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ የውሃ አካላት ላይ ጉዳት እያደረሰ ያለውን የእምቦጭ አረም ለመከላከል አገራዊ እውቀትን መሰረት ያደረጉ ሥራዎች መስራት ፋይዳው የጎላ መሆኑንም አመልክተዋል።
"አገር በቀል የጸረ እምቦጭ መድኃኒት ግኝትም የእምቦጭ አረምን ለማጥፋት አገር በቀል የምርምር ውጤትን ይዞ መቅረብ ወቅቱ የሚጠይቀው መፍትሄ ስለመሆኑ ማሳያ ነው" ሲሉም ዶክተር ታደለ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሊቃውንትና ምሁራን ማህበር አገር በቀል የምርምር ሥራዎችን ለማሳደግ የሚያደርገውን ጥረት የጤና ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንዲሁም ሌሎች ተቋማትም እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል።
የአገር በቀል የጸረ-እምቦጭ መድኃኒት ግኝቱ ባለቤት የሆኑት የአገር በቀል እውቀት ተመራማሪው መሪጌታ በላይ አዳነ በበኩላቸው፣ መድኃኒቱ ከአንድ የፅጽዋት ፍሬ እንደሚቀመምና ጥቅም ላይ ሲውልም ተጓዳኝ ችግር እንደማያስከትል ተናግረዋል።
"መድኃኒቱ በ24 ሰዓታት ውስጥ እምቦጭን 70 በመቶ ያመክናል፤ በ30 ቀናት ውስጥ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ማድረቅ ይችላል" ብለዋል።
በተጨማሪም በውሃ ውስጥ በሚገኙ ብዝሃ-ህይወት ላይ ጉዳት ሳያስከትል የደረቀው እምቦጭ ለእንስሳት ምግብነት እንደሚውል ነው ያስረዱት።
እንደ መሪጌታ በላይ ገለጻ፣ በአሁኑ ወቅት ለመድኃኒት ቅመማ የሚሆን እጽዋት ማልሚያ መሬት ከመንግስት አስፈቅደው በመስራት ላይ ይገኛሉ።
አገር በቀል የጸረ-እምቦጭ የምርምር ግኝቱን በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር ለማስገባት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ድግሞ የማህበሩ ሥራ እስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ባብዬ ናቸው።
ከሥራዎቹ መካከል ግኝቱን በአዕምሯዊ ንብረትነት ማስመዝገብ፣ መድኃኒቱ ጥቅም ላይ ሲውልም በስፋት መርጨት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን የማመቻቸት ሥራዎች እንደሚጠቀሱ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሊቃውንትና ምሁራን ማህበር በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 በሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅት የተመዘገበ ሲሆን፣ ኢትዮጵያዊያን ሊቃውንትና ምሁራንን በማሰባሰብ በአገር በቀል እውቀቶች ምርምር ላይ የሚሰራ ማህበር ነው።