ቀጥታ፡

የሃይማኖት ተቋማት ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት አለባቸው

አዲስ አበባ መስከረም 12/2013 (ኢዜአ) የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከጤና ሚንስቴር እና ከብሔራዊ የኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት ጋር ኤች.አይ.ቪ/ ኤድስን ለመከላከል የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ።

የእምነት አባቶች የኤች.አይ.ቪን ስርጭት ለመከላከል በሚደረገው ጥረት መንፈሳዊና አባታዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ዶክተር ሊያ ጥሪ አቅርበዋል።

የጤና ሚንስትሯ ዶክተር ሊያ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ የማህበረሰብ ጤና ችግር ሆኖ እንዳይቀጥል የመስራት ጉዳይ የአገር ህልውና ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል።

"ኢትዮጵያ ከአብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት በተሻለ ሁኔታ የቫይረሱን ስርጭት በመግታቷ የብዙዎችን ትኩረት መሳብ ችላለች" ብለዋል።

ይሁን እንጂ የተመዘገበውን ውጤት ተከትሎ በተፈጠረው መዘናጋት እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ ወረርሽኙ ዳግም እየተባባሰ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

በአንዳንድ የሃይማኖት አስተማሪዎች ዘንድ ሰዎች የጸረ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መድኃኒትን እንዳይጠቀሙ የሚገፋፉ መልዕክቶች ሲተላለፉ የሚስተዋልበት አጋጣሚ መኖሩንም ጠቁመዋል።

እንደሚኒስትሯ ገለጻ ወረርሽኙን ለመከላከል የእምነት ተቋማትና የሃይማኖት አባቶች ለእምነቱ ተከታዮች የሚያስተምሩት ትምህርትና ተግሳጽ ተቀባይነቱ የጎላ ነው።

በመሆኑም በጸረ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መድኃኒት አጠቃቀም በኩል የሚታዩ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ ህብረተሰቡ ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የእምነት አባቶች እየተስፋፋ የመጣውን የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ስርጭት ለመከላከል መንፈሳዊና አባታዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ዶክተር ሊያ ጥሪ አቅርበዋል።

የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጽጌረዳ ክፍሌ በበኩላቸው ኤች.አይ.ቪ ኤድስ አሁንም አገራዊ ስጋት መሆኑን ገልጸዋል።

የሃይማኖት ተቋማት ወረርሽኙን ለመከላከል ሲያደርጉት የነበረው እንቅስቃሴ እየተቀዛቀዘ መምጣቱን የጠቆሙት ዳይሬክተሯ፣ በክልል ከተሞች በተለይ በአዲስ አበባ ስርጭቱ ከፍተኛ ደረጀ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

የሃይማኖት ተቋማት ከዚህ ቀደም ወረርሽኙን ለመከላከል ሲያደርጓቸው የነበሩ ጥረቶችን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

አጋላጭ ባህሪ የሚታይባቸውንና ተጋላጭ የሆኑ ወጣቶች ተከታታይ ሃይማኖታዊና አባታዊ ምክርና ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ማነጽ እንዳለባቸውም ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

ጉባኤው ባለፉት ዓመታት የወረርሽኙን ስርጭት ለመቀነስ በተደረጉ እንቅስቃሴዎች የማይናቅ አስተዋጽኦ እንደነበረው የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሀን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ናቸው።

ካለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ወዲህ እንደገና የመጨመር አዝማመሚያ እያሳየ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ትውልድን የማዳን ተግባር በትኩረት እንደሚሰራም አክለዋል።

ጉባኤው በ2013 በጀት ዓመትም ትርጉም ያለው ሥራ ለመስራት እንዲችል ከአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት የ17 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማግኘቱንም ገልጸዋል።

የጉባኤው የበላይ ጠባቂዎችም አማኞች ራሳቸውን ለበሽታው ከሚያጋልጡ ተግባራት ራሳቸውን ሊያቅቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሃይማኖት አባቶችም ግንዛቤ በመስጠት፣ የጤና ባለሙያዎችን ምክር በማዳመጥ በጋራ ጤናማ ዜጋ ለመፍጠር መረባረብ እንዳለባቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም