ቀጥታ፡

የፖሊስ አባላት ለህግ የበላይነት መረጋገጥ ኃላፊነታቸውን በብቃት ሊወጡ እንደሚገባ ተመለከተ

አምቦ መስከረም 12/2013 (ኢዜአ) የፖሊስ አባላት ከወገንተኝነት የፀዳ አገልግሎት በመስጠት የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ኃላፊነታቸውን በብቃት ሊወጡ እንደሚገባ ተመለከተ። 

በምዕራብ ሸዋ ዞንና አምቦ ከተማ አስተዳደር ሰላምንና ህግን በማስከበር የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ 557 የፖሊስ አባላት የማዕረግ ዕድገት ተሰጣቸው።

የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ጎሳዬ ከበደ በስነስርዓቱ ወቅት እንደገለጹት  የማዕረግ ዕድገት  የተሰጠው የፖሊስ አባላት ሰላምንና ህግን በማስከበር የላቀ አስተዋፅኦ ያበረከቱ እንዲሁም ከ15 ዓመታት  በላይ ያገለገሉ ናቸው፡፡

ለህብረተሰቡ ከወገንተኝነት የፀዳ አገልግሎት በመስጠት ለህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የፖሊስ አባላት ኃላፊነታቸውን በብቃት ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

"ፖሊስ ሕገ መንግስቱን በማክበርና በማስከበር በህዝብና በመንግስት የተጣለበትን ኃላፊነት በቅንነት፣ በታማኝነትና በብቃት መወጣት ይጠበቅበታል" ብለዋል፡፡

የማዕረግ እድገቱ ለበለጠ ስራ የሚያነሳሳችሁ በመሆኑም  ውጤታማ የስራ አፈጻጸም ለማስመዝገብ መስራት እንደላባቸውም ተናግረዋል።

የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ድርርሳ ዋቁማ በበኩላቸው ህብረተሰቡ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ጠንክራችሁ መስራት ይጠበቅባችኋል ብለዋል።

የህግ የበላይነት እንዳይከበር እንቅፋት የሚሆኑትን አካላትን ስርዓት ማሲያዝ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

ለፖሊስ አባላቱ የማዕረግ ዕድገት የተሰጣቸው የኦሮሚያ ልዩ ዞን ልዩ ኃይል ኃላፊ ኮማንደር ሻሎ ገለታ በተገኙበት ነው፡፡

ከመካከላቸውም 149 ሴቶች ናቸው።

የማዕረግ እድገቱ የስራ አፈጻጸም ብቃትን፣ የትምህርት ዝግጅትንና አካላዊ ብቃትን እንዲሁም ጥሩ ስነምግባርን ታሳቢ ያደረገ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም