ተመድ የጤናማ እጆች የኢትዮጵያ ጥምረት መነሻ የሚሆን የ500 ሺህ ዶላር ድጋፍ አደርጋለሁ አለ - ኢዜአ አማርኛ
ተመድ የጤናማ እጆች የኢትዮጵያ ጥምረት መነሻ የሚሆን የ500 ሺህ ዶላር ድጋፍ አደርጋለሁ አለ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 12/2013(ኢዜአ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም /ዩኤንዲፒ/ ለ'የጤናማ እጆች የኢትዮጵያ ጥምረት' መነሻ የ500 ሺህ ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ።
ጥምረቱ ኮቪድ-19ን መከላከያና መቆጣጠሪያ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ማግኘትና እጅን መታጠብ ወረርሽኙን ለመከላከል ያለውን ፋይዳ ማስተማርን ዓላማ አድርጎ የተቋቋመ ነው።
መንግስት፣ የግሉ ዘርፍና የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች በጥምረቱ ውስጥ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ናቸው።
የመንግስታቱ ድርጅት የልማት ፕሮግራም /ዩኤንዲፒ/ ጥምረቱን መቀላቀሉን ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
ጥምረቱ ለወረርሽኙ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስና ቫይረሱን መከላከል የሚያስችሉ የጤና መረጃዎችን ተደራሽ ማድረግን ትኩረቱ አድርጎ ይሰራል።
የግሉ ዘርፍ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ምርትና ከመንግስት ቁሳቁሱን የማሰራጨት አቅም አጣምሮ ስርዓት በመዘርጋት የጥምረቱ ስራዎች ይከወናሉ።
የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኅብረተሰቡ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከል ላይ የባህሪይ ለውጥ እንዲያመጣ፤ ለዚህም የተለያዩ የተግባቦት ማስተላለፊያ አማራጮችን በማዘጋጀት ያስተምራሉ።
የልማት ፕሮግራሙ በማኅበራዊና በከባቢ አየር ጉዳዮች ላይ በሚሰራው "ዳልበርግ ካታሊስት" በተሰኘ ተቋም በኩል የጤናማ እጆች የኢትዮጵያ ጥምረት መነሻ የ500 ሺህ ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
ድጋፉ በአዲስ አበባ የንጽህና መጠበቂያ እንዲሁም ለማስተማሪያ የሚውሉ የተግባቦት ቁሳቁስ /ኮሙኒኬሽን ማቴሪያልስ/ ወጪና ስርጭትን አስመልክቶ ለሚሰሩ ስራዎች እንደሚውል አመልክቷል።
ለወረርሽኙ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችና በተጨማሪም የዜጎች ስራና ኑሮ እንዲቀጥል ለማድረግ ለሚከናወኑ ተግባራትም እንዲሁ።
ለጥምረቱ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው የተባለው።
የተመድ የልማት ፕሮግራም ከጥምረቱ ጋር ያለው ትብብር ድርጅቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያደርሳቸውን ጉዳቶች ለመቀነስ እየሰጠ ያለው ምላሽ አካል እንደሆነም በመግለጫው ተጠቁሟል።
የልማት ፕሮግራሙ ለኢትዮጵያ የሚያደርገው የኮቪድ-19 ስትራቴጂያዊ ድጋፍ የኢትዮጵያ መንግስት ወሳኝ የሚባሉ የንግድ ስራዎች እንዲቀጥሉ የቴክኒክና የቁሳቁስ ድጋፎችን ማድረግ ላይ ያተኮረ እንደሆነ አስታውቋል።
በድጋፉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ ኤጀንሲዎች፣ የክልል መንግስታትና የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተጠቃሚዎች መሆናቸውንም አመልክቷል።
ኢትዮጵያ በመጋቢት 2012 ዓ.ም በዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም የቀረበውን የጤናማ እጆች ጥሪ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አማካኝነት መቀበሏ ይታወቃል።
የቀረበው ጥሪ እጅን በውሃና በሳሙና በመታጠብ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን እንከላከል የሚል ነው።